ተጠባቂው የለንደን ማራቶን 2020 በኢትዮጵያዊው አትሌት አሸናፊነት ተጠናቀቀ
ቀነኒሳ በቀለ በነገረኝ መንገድ ሮጬ ነው ያሸነፍኩት-ሹራ ቂጣታ
በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የለንደን ማራቶን ከ 2 ዓመት በፊት ውድድሩን 2ኛ ሆኖ ባጠናቀቀው በኢትዮጵያዊው ሹራ ቂጣታ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ሹራ 2:05:41 በሆነ ሰዓት በመግባት ነው ውድድሩን በአንደኛነት ያሸነፈው፡፡ አትሌቱ ከድሉ በኋላ በሰጠው አስተያየት “ለዚህ ሩጫ ቀነኒሳ በቀለ ሲረዳኝ ነበር፡፡ እንዴት መሮጥ እንዳለብኝ መክሮኛል ፤ በዚሁ መንገድ ተለማምጄ በማሸነፌ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብሏል፡፡
ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ሲሳይ ለማ ኬንያዊውን ቪንሰንት ኪፕቹምባን ተከትሎ 3ኛ ወጥቷል፡፡
በውድድሩ ከቀነኒሳ ጋር ጥብቅ ፉክክርን እንደሚያደርግ ሲጠበቅ የነበረው ኤሉድ ኪፕቾጌ ከአሸናፊው በአንድ ደቂቃ ያህል ዘግይቶ በ2:06:39 8ኛ ሆኖ ውድድሩን አጠናቋል፡፡ “በጣም ከፍቶኛል ፤ ለመጨረሻዎቹ 15 ኪሎ ሜትሮች የቀኝ ጆሮዬ ላይ ችግር ነበረብኝ ፤ የአየር ሁኔታውም ቀዝቃዛ ነበር ፤ ቢሆንም ይሔን ምክንያት አላደርግም፡፡ ከዚህ በኋላ ብዙ ማራቶኖች አሉ ፤ ተመልሼ እመጣለሁ” ሲል የማራቶን ክብረ-ወሰን ባለቤቱ ኤሉድ ኪፕቾጌ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ኢትዮጵያውያን በደመቁበት በዚህ ውድድር ብርቱ ፉክክር ያደረጉት ሞስነት ገረመው ፣ ሙሌ ዋሲሁን እና ታምራት ቶላ በቅደም ተከተል ከ4ኛ-6ኛ ወጥተዋል፡፡
የአሸናፊነቱን ቅድመ ግምት አግኝቶ የነበረው ቀነኒሳ በጉዳት ምክንያት ከውድድሩ ውጭ ለመሆን መገደዱን መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡
በሴቶቹ ደግሞ ውድድሩን ኬንያዊቷ የክብረ-ወሰኑ ባለቤት ብሪጅ ኮስጌ የአምና ድሏን አስጠብቃ በ 2:18:58 አሸንፋለች፡፡
አሜሪካዊቷ ሳራ ሆል 2ኛ ሌላዋ ኬኒያዊት ሩት ቼፕንጌቲች ደግሞ 3ተኛ ሆነው ሲያጠናቅቁ ኢትዮጵያውያኑ አሸቴ በከሪ እና መገርቱ አለሙ 4ኛና 5ኛ ሆነው ውድድራቸውን ጨርሰዋል፡፡