አዲሱ ቴክኖሎጂ ሰዎች ከሞቱ በኋላ ዳግም ህይወት ሊዘሩ ይችላሉ በሚል የተፈጠረ ነው
አዲሱ የሞት ማምለጫ ቴክኖሎጂ ይሳካለት ይሆን?
የሰው ልጅ በየጊዜው ህይወትን ቀለል የሚያደርጉ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል።
በእስካሁኑ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች አስደማሚ እና ሊሆን አይችልም የተባሉ ፈጠራዎች በሰው ልጆች ተሰርተዋል።
ይሁንና እስካሁን ሞትን ማምለጥ የሚያስችሉ ፈጠራዎችን መስራት ያልተቻለ ሲሆን ቱሞሮ ባዮ የተሰኘ ኩባንያ ግን ባልተሞከረውን መንገድ እየሄደ ይገኛል።
ይህ ኩባንያ አንድ ቀን ይሳካልኝ ይሆናል በሚል መሞታቸው በሐኪሞች የተረጋገጡ ሰዎችን አስከሬን በማጠራቀም ላይ ነው።
የዚህ ኩባንያ ዓላማ ሰዎች ህይወታቸው ከላፈ በኋላ በበጎ ፈቃደኝነት አስከሬናቸውን እንዲሰጡት ካደረገ በኋላ ወደ ማቀዝቀዣ ቦታ ይወስዳል።
የአስከሬኑ ቅዝቃዜ ዜሮ ድግሪ ሴንትግሬድ ከደረሰ በኋላ አስከሬኑ በቅዝቃዜ እና በሌሎች ተፈጥሯዊ ምክንያቶች እንዳይበሰብስ የሚያደርግ የተለያዩ ኬሚካሎችን ተጠቅሞ ባለበት እንዲቆይ ያዱርጋል።
ኩባንያው ይህን የሚያደርገው ሟቾች ወደ ዳግም ህይወት መመለስ ይቻላል የሚል ዕምነት ስላለው እና ሰዎችም ረጅም እድሜ በህይወት የመኖር ፍላጎት አላቸው በሚል ነው።
ሰዎች ይህን አገልግሎት ለማግኘት 200 ሺህ ዶላር መክፈል የሚጠበቅባቸው ሲሆን አብዛኞቹ ከፋዮች ምን አልባት ቴክኖሎጂው ከሰራ ብለው የሚያምኑ ናቸው ተብሏል።
ከኩባንያው መስራች አንዱ የሆኑት ኢምል ኬንድዚዮራ ለቢቢሲ እንዳሉት ሀሳቡ የተጀመረው አንዲት ስዊድናዊ በልብ ህመም ህይወቷ አልፏል ተብሎ በማቀዝቀዣ ውስጥ ከቆየት ከሁለት ሰዓት በኋላ ዳግም ዳግም ህይወት መዝራቷን ተከትሎ ነው ብለዋል።
እንዲሁም የሞተ የአይጥ አዕምሮን በዚህ የማቀዝቀዝ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ዳግም እንዲመለስ እና በቀዶ ጥገና መልክ በሌላ አይጥ ካይ ተገጥሞ መስራቱ እንደተረጋገጠም ተገልጿል።
ይህ ተስፋ ሰጪ ምልክት በሰዎች ላይ ሊሰራ ይችላል በሚል እየሞከርነው ነው የሚሉት የኩባንያው መስራች የደንበኞቻቸው ቁጥር እየጨመረ እንደሆነም ተናግረዋል።
በተለይም በኮሮና ቫይረስ ወቅት ሞት ከመቼውም ጊዜ በላይ ቅርብ መሆኑን ተከትሎ ከቫይረሱ መከሰት በኋላ የደንበኞቻቸው ቁጥር ጨምሯልም ተብሏል።
የአንድን የሰውነት አካል በቀዶ ህክምና ወደ ሌላ ሰው መተከት ህክምና ሲጀመር ሰዎች ብዙ ተገርመው ነበር የተባለ ሲሆን ምን አልባት ከ10 ወይም ከ100 ዓመት በኋላ የሞቱ ሰዎችን ዳግም ወደ ህይወት መመለስ ሊጀመር እንደሚችልም ተስፋ ተደርጓል።