የእንጀራ ልጁን ለ10 ዓመታት አስገድዶ ሲደፍር ቆይቶ የገደላት ግለሰብ ሞት ተፈረደበት
ተከሳሹ የሟች እንጀራ አባት ሲሆን ከ10 ዓመት እድሜዋ ጀምሮ አስገድዶ ሲደፍራት ቆይቷል
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተከሳሹን ጥፈተኛ በማለት በሞት እንዲቀጣ ወስኗል
በአዲስ አበባ የእንጀራ ልጁን ከ10 ዓመት እድሜዋ ጀምሮ ለ10 ዓመታት አስድዶ ሲደፍር ቆይቶ የገደላት ግለሰብ በሞት እንዲቀጣ መወሰኑን የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚካኤል ሽመልስ ጌታሁን የተባለ ተከሳሽ የእንጀራ ልጁ ሆነችውን ሟች አዶናዊት ይሄይስ በበአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ልዩ ቦታው 15 ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ከ10 ዓመቷ ጀምሮ አስገድዶ ስደፍራት መቆየቱ ተነግሯል።
ተከሳሹ ሟች አዶናዊት ይሄይስን “ከተናገርሽ እናትሽና አባትሽን እገላለሁ” እንዲሁም “የግብረ ስጋ ግኑኝነት ስንፈፅም በሞባይል ቪድዮ ቀርጨዋለሁ፤ በሚድያና በቴሌግራም እለቀዋለሁ” በማለት እያስፈራራ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ህይወትዋ እስካለፈበት ድረስ በተደጋጋሚ አስገድዶ መድፈር እንደፈጸመ ተነግሯል።
ሟች አዶናዊት ይሄይስ ከተከሳሽ ሁለት ጊዜ እርገዛ የነበረ ሲሆን፤ መጀመሪያ የነበረው እርግዝና ቤተሰብ እንዳያውቅበት የሟች ስም ኤፍራታ አለማየሁ በሚልና የሟች ዕድሜም 19 ዓመት እንደሆነ በማስመሰል ሐሰተኛ ስም እና ዕድሜ በማስመዝገብ ያረገዘችውን ፅንስ እንድታስወርድ ማስገደዱም በክሱ ተመላክቷል።
መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም ተከሳሽ በሟች ላይ በፈፀመው የአስደግጎ መድፈር ወንጀል ምክንያት ፖሊሶች ሊያዙት ወደ ቤቱ መምጣታቸውን ሲያይ አምልጦ ከሄደ በኃላ ፖሊሶች መሄዳቸው ሲያረጋግጥ ተመልሶ ወደ ሟች ቤት በመምጣት ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ወላጅ እናትዋ ፊት ህይወትዋ እንዲያልፍ አድርጓል ይላ ክሱ።
ሟች ሕይወትዋ ሲያልፍም ለሁለተኛ ጊዜ ከተከሳሽ እርጉዝ እንደነበረችም በክሱ ተመላክቷል።
ክሱን የተመለከተው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የሰው ግድያና ውንብድና ችሎት በትናንትናው እለት ታህሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ሚካኤል ሽመልስ ጌታሁን በሞት እንዲቀጣ እንደወሰነ ከሚኒስቴሩ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡