አቶ ቡልቻ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የገንዘብ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል
አንጋፋው ፖለቲከኛ እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።
በ1923 ዓ.ም. የተወለዱት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ነበራቸው ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የገንዘብ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።
እንዲሁም የዓለም ባንክ የአፍሪካ ተወካይ በመሆን የሰሩት አቶ ቡልቻ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቀጥረው በተለያዩ ሀገራት አገልግለዋል።
በምጣኔ ሀብቱ ያካበቱትን ልምድ በመያዝም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ እንቅስቃሴን በማድረግም ይታወቃሉ።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራቲክ ንቅናቄን በመመሥረት እና ሊቀመንበር በመሆን በፖለቲካው ላይ የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል።
በ1997 ዓ.ም ፓርቲያቸውን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራቲክ ንቅናቄን ወክለው በፓርላማ አባልነት ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል።
አቶ ቡልቻ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ባለገሉበት ወቅት በተለይም የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን በመሞገት ይታወቁ ነበር።
አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በዘመናዊ የግል ንግድ ባንኮች ምሥረታ ታሪክ ተጠቃሽ የሆነው የአዋሽ ባንክ መሥራች ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት “በሚችሉት ሁሉ ሀገራቸውንና አፍሪካን ያገለገሉ፣ በአቋማቸው ጽኑ፣ ሕዝቦችን ለማቀራረብ የተጉ፣ እውነት ነው ብለው ያመኑትን የትምና መቼም የሚናገሩ ነበሩ” ብለዋል።
እንዲህ ዓይነት ብርቱ የሀገር ሽማግሌዎችን ማጣት ጉዳቱ ለሀገር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይቀበላት” ብለዋል፡፡
አቶ ቡልቻ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቦጂ ቢርመጂ ወረዳ ከአባታቸው አቶ ደመቅሳ ሰንበቶ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ናሲሴ ሰርዳ በ1923 ዓ.ም ነው ተወለዱት።