በቻይና 35 ሰዎችን በመኪና ገጭቶ የገደለው ግለሰብ የሞት ፍርድ ተፈረደበት
የ62 አመቱ ግለሰብ የስፖርት ማዕከል ውስጥ ጥሶ በመግባት ባደረሰው ጥቃት ነው ቅጣቱ የተላለፈበት
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በቻይና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያነጣጠሩ ድንገተኛ ጥቃቶች እየተበራከቱ ነው
ፋን ዋኪዩ የተባለው የ62 አመት ቻይናዊ ባለፈው ወር በደቡባዊ ቻይና በሚገኝ የስፖርት ማዕከል ውስጥ በመኪና ጥሶ በመግባት 35 ሰዎችን ገጭቶ ህይዎት ማጥፋቱ በቅርቡ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በዙሀይ ከተማ የደረሰው ጥቃት በሀገሪቱ በአስር አመታት ውስጥ በህዝብ ላይ ከተፈጸሙ አስከፊ ጥቃቶች መካከል አንዱ ነው፡፡
ግለሰቡ በፍርድ ቤት ውሳኔ ትዳሩ መፍረሱን ተከትሎ በውሳኔው በመቆጣት መኪናውን እያሽከረከረ ውጭ ላይ ስፖርት ሲሰሩ በነበሩ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡
ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላ በስለት ራሱን ለማጥፋት ባደረገው ሙከራ ጉዳት ደርሶበት የነበረው ፋን ዋኪዩ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ህክምና ሲደረግለት ቆይቷል፡፡
ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው ፍርድ ቤት በትላንትናው ዕለት ግለሰቡ በሞት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡
ፍርድ ቤቱ “የተከሳሹ ፋን ዊኪዩ የወንጀል ባህሪ በከፍተኛ ጨካኔ የተሞላ እና ምንም አይነት በደል ባልፈጸሙ ንጹሀን ላይ የተፈጸመ በመሆኑ አስተማሪ እንዲሆን ከፍተኛውን ቅጣት እንዲቀጣ ወስኛለሁ” ብሏል፡፡
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዢንፒንግ በህዳር 11 ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ “አውሬነት የተሞላበት ድርጊት” በሚል ያወገዙት ሲሆን ጥፋተኛው ተገቢው ቅጣት እንዲተላለፍበትም ጥሪ አድርገው ነበር ፡፡
ጥቃቱ ከ2014 ወዲህ የብዙ ሰዎችን ህይወት የነጠቀ በአይነቱ የተለየ ጥቃት መሆኑን የቻይና የፍትህ ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡
ቻይና በቅርብ ጊዜያት ህጻናትን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያነጣጠረ ድንገተኛ ጥቃት እየተበራከተባት ይገኛል፡፡
ከቀናት በፊትም በተመሳሳይ አንድ ግለሰብ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በመኪና ጥሶ በመግባት 18 ተማሪዎችን ጨምሮ በ30 ሰዎች ላይ ጉዳት በማድረስ በፈጸመው ወንጀል የቅጣት ውሳኔውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ በጀርመን በገና በአል ሸመታ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በተፈጸመ የመኪና ጥቃት 5 ሰዎች ሲሞቱ ከ200 በላይ ሰዎች መጎዳታቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡