7 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ወጥቶበት የነበረው የሂዝቦላህ አመራር በእስራኤል ጦር ተገደለ
ኢብራሂም አኪል ራድዋን የተሰኘውን የሂዝቦላው ተዋጊ ሀይል የሚመራ አመራር የነበረ ሲሆን አሜሪካ ከዚህ በፊት ያለበትን ለጠቆመኝ 7 ሚሊዮን ዶላር እከፍላለሁ ብላ ነበር
የእስራኤል ጦር በሊባኖስ መዲና ቤሩት ባደረሰው የአየር ላይ ጥቃት ኢብራሂምን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ሲገደሉ 59 ሰዎች ቆስለዋል
7 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ወጥቶበት የነበረው የሂዝቦላህ አመራር በእስራኤል ጦር ተገደለ፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት የሐማስ ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት መልኩን ቀይሮ አሁን ላይ ወደ ሊባኖስ ፊቱን አዙሯል፡፡
የእስራኤል ጦር ከትናንት ጀምሮ በደቡባዊ ሊባኖስ በኩል ከፍተኛ የተባለ ጥቃት በማድረስ ላይ ሲሆን ከደቂቃዎች በፊት በሀገሪቱ መዲና ቤሩት የአየር ለይ ጥቃት ሰንዝራለች፡፡
በዚህ ጥቃት ከዚህ በፊት በአሜሪካ ይፈለግ የነበረው የሂዝቦላህ ሬድዋን ሀይል ኮማንደር የሆነው ኢብራሂም አኪል መገደሉን ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ከኢብራሂም አኪል በተጨማሪ ስምንት ሰዎች ሲገደሉ 60 ሰዎች ገደማ ደግሞ ቆስለዋል፡፡
እስራኤል የሂዝቦላህ ከፍተኛ አመራር መካከል ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ላይ ፉአድ ሽኩርን በደቡባዊ ሊባኖስ መግደሏ ይታወሳል፡፡
ኢብራሂም በፈረንጆቹ 1983 ላይ በቤሩት በሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ በደረሰው የቦምብ ጥቃት እንዲሁም በዚሁ ተመሳሳይ ዓመት በሊባኖስ የነበሩ የአሜሪካ ባህር አባላት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አቀነባብሯል ተብሎ ይፈለግ ነበር፡፡
በመላው ሊባኖስ የኮሙንኬሽን መሳሪያዎች መፈንዳታቸውን ተከትሎ ከ37 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከዚህ ሴራ ጀርባ እስራኤል እጇ እንዳለበት ሂዝቦላህ ገልጿል፡፡
ፍንዳታዎቹን ተከትሎ ሊባኖሳዊያን በእጃቸው እና ቤታቸው ውስጥ ያሉ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እየጣሉ ነው ተብሏል፡፡