በመካከለኛው ምስራቅ ያሉት የአሜሪካ የጦር መርከቦች ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሚችል ተሰግቷል
ሂዝቦላህ ሩሲያ ሰራሽ የጦር መርከብ ማጥቃት የሚችል ሚሳኤል መታጠቁ ተገለጸ፡፡
ሐማስ ያልተጠበቀ ጥቃት በእስራኤል ላይ ማድረሱን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት 32ኛ ቀኑ ላይ የሚገኝ ሲሆን እስራኤል በአየር እና በምድር ላይ ጥቃቷን በጋዛ እያካሄደች ትገኛለች፡፡
የሊባኖሱ ሂዝቦላህ እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጠየማዊያን ላይ የጀመረችውን ጥቃት ካላቆመች ጦርነቱ ወደ አካባቢው ሀገራት ሊዛመት እንደሚችል ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል፡፡
አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎችም ሀገራት የእስራኤል ፍልስጤም ጦርነት ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዳይዛመት ይፈልጋሉ ቢባልም ዋሸንግተን እስራኤልን ከመደገፍ እንድትታቀብ ሲያሳስቡ ቆይተዋል፡፡
ይሁንና አሜሪካ ለእስራኤል የቀጥታ ድጋፍ ማድረጓን ተከትሎ በሶሪያ እና ኢራቅ ያሏት የጦር ሰፈሮች ጥቃት ተሰንዝሮባታል፡፡
ዋሸንግተን ለደረሰባት ጥቃት የአጸፋ ምላሽ የሰጠች ሲሆን በዛሬው ዕለት በሶሪያ ያሉ የኢራንን የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ማድረሷ ተገልጿል፡፡
ሂዝቦላህ በአውሮፓ ሀገራት የተከማቹ ፈንጂዎች እንዳሉት አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ተናገሩ
ይህ በዚህ እንዳለም የሊባኖሱ ሂዝቦላህ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን እንደታጠቀ ገልጾ በመካከለኛው ምስራቅ ባሉ የጦር መርከቦች ላይ ጥቃት ሊያደርስ እንደሚችል ዝቷል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ሂዝቦላህ ሩሲያ ሰራሹ ያኮንት የተሰኘው የጦር መርከቦችን ለማውደም የሚውለው ሚሳኤል እንደታጠቀ ተገልጿል፡፡
ይህ ሚሳኤል ከአየር ላይ፣ ከየብስ እና ከባህር ላይ መተኮስ የሚችል ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ሲሆን ከዓመታት በፊት የሩሲያ ጦር ወደ ሶሪያ በገባበት ወቅት ሂዝቦላህ እጅ ገብቷልም ተብሏል፡፡
እስከ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ያሉ ኢላማዎችን መምታት ይችላል የተባለው ይህ ሚሳኤል በሜድትራኒያን ባህር ላይ ያሉ የአሜሪካ የጦር መርከቦች ላይ ጥቃት ሊፈጽም እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ለዓመታት ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ሲያከማች ነበር የተባለው ሂዝቦላህ ከኢራንም የተለያዩ ድጋፎችን እያገኘ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በእስራኤል ጦር የተገደሉ ፍልስጤማዊያን ቁጥር ከ10 ሺህ ያለፈ ሲሆን በየዕለቱም 150 ህጻናት እየተገደሉ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
የየመኑ ሁቲ አማጺ ቡድን የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላንን መትቶ መጣሉን የገለጸ ሲሆን አሜሪካ ለእስራኤል ድጋፍ ማድረጓን እንድታቆምም አስጠንቅቋል፡፡