ሂዝቦላህ በአውሮፓ ሀገራት የተከማቹ ፈንጂዎች እንዳሉት አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ተናገሩ
ከአውሮፐውያኑ 2012 ጀምሮ በተለያዩ የአውሮፓ መጋዘኖች ፈንጂዎች ሲከማቹ እንደነበር ባለሥልጣኑ አንስተዋል
በቤይሩት ፈንድቶ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው አሞኒየም ናይትሬት በሂዝቦላህ የተዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል
ሂዝቦላህ በአውሮፓ ሀገራት የተከማቹ ፈንጂዎች እንዳሉት አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ተናገሩ
ሂዝቦላህ አሞኒየም ናይትሬትን ጨምሮ የተለያዩ ፈንጂዎችን ወደ አውሮፓ በማስገባት ከእርሱ ጋር ግንኙነት ባላቸው መጋዘኖች ማከማቸቱንአንድ የዩኤስ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባለስልጣን ይፋ አድርገዋል፡፡
መጋዘኖቹ ከውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት በኢራን በሚደገፉ ቡድኖች የተቋቋሙ መሆናቸውን የገለጹት ባለሥልጣኑ ፣ በሊባኖስ ቤይሩት ፈንድቶ በትንሹ 190 ሰዎችን ለሞት በመዳረግ ከ 6,500 በላይ የቆሰለውን አሞሞን ናይትሬትን ጨምሮ ሌሎች ፈንጂዎችም እንደሚገኙባቸው ነው የገለጹት፡፡
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የፀረ-ሽብርተኝነት አስተባባሪ የሆኑት ናታን ሳሌሰ “ዛሬ የአሜሪካ መንግስት ሂዝቦላህ በአውሮፓ ስለመገኘቱ አዳዲስ መረጃዎችን ይፋ እያደረገ ነው” ብለዋል ፡፡
እ.ኤ.አ. ከ 2012 አንስቶ ሂዝቦላህ በአውሮፓ የአሞኒየም ናይትሬት መሸጎጫዎችን ስለማቋቋሙ ያነሱት ናታን “እንደዚህ ዓይነቶቹ መሸጎጫዎች በቤልጅየም ፣ፈረንሳይ ፣ ግሪክ ፣ ጣሊያን ፣ እስፔን እና ስዊዘርላንድ ስለመኖራቸው መግለጽ እችላለሁ” ስለማለታቸውም ዘ ናሺናል ዘግቧል፡፡
በፈረንሳይ ፣ ግሪክ እና ጣሊያን ከፍተኛ መጠን ያለው አሞኒየም ናይትሬት ስለመገኘቱ አሊያም ስለመወገዱም ነው ያብራሩት፡፡
መረጃው እንዴት እንደተገኘ ባይገልጹም ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በሌሎችም የአውሮፓ ሀገራት ሂዝቦላህ የተለያዩ ፈንጂዎችን ስለማከማቸቱ ግን ባለሥልጣኑ አብራርተዋል፡፡ በቤይሩት ስለተከሰተው ፍንዳታ ግልጽ እና ሰፊ ምርመራ እንዲደረግም አሜሪካ ጥሪ አቅርባለች፡፡
ኬሚካሉ በቤይሩት ወደብ ተከማችቶ የቆየው በሂዝቦላህ አማካኝነት እንደሆነና የቴህራን አለቆቻቸው ትእዛዝ በሰጧቸው ጊዜ ከፍተኛ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም አቅደው ያዘጋጁት ስለመሆኑ ናታን በንግግራቸው አንስተዋል፡፡
በቤይሩት በተከሰተው ፍንዳታ የተነሳው እሳት
የአሞኒየም ናይትሬት በተለምዶ በኢንዱስትሪ እና ለግብርና እንደ ማዳበሪያ ከማገልገሉ ባለፈ ለዝቅተኛ ደረጃ ፈንጂ ስራም ይውላል፡፡
ነገር ግን ከፍተኛ ክምችት ያለው አሞኒየም ናይትሬት በቤይሩት ወደብ እንደተከሰተው ፍንዳታ ከፍተኛ ውድመት ያስከትላል፡፡