ቱርክ ወደ አውሮፖ ህብረት እንድትገባ የሚፈቀድላት ከሆነ የስዊድንን የኔቶ አባልነት ልታጸድቅ ትችላለች- ኤርዶጋን
ኤርዶጋን እና የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስቴር ኡልፍ ክሪስተርስን በሉታኒያው የኔቶ ስብሰባ ይገናኛሉ ተብሏል
ቱርክ የአውሮፖ ህብረት አባል ለመሆን በመጠበቅ 50 አመታት ማስቆጠሯን እና ሁሉም የአውሮፖ የኔቶ አባላት የአውሮፖ ህብረት አባል ናቸው ብለዋል ኤርዶጋን
የቱርኩ ፕሬዝደንት ኤርዶጋን እንደተናገሩት አውሮፖውያን ቱርክ ወደ አውሮፖ ህብረት እንድትገባ የሚፈቅዱላት ከሆነ ቱርክም የስዊድንን የኔቶ አባልነት ጥያቄ ልታጸድቅ ትችላለች ብለዋል።
የስዊድንን ኔቶን የመቀላቀል ጥያቄ የገታችው ቱርክ ፕሬዝደንት ኤርዶጋን ይህን ያሉት በሉታኒያ ለሚደደረገው የኔቶ ስብሰባ ከመሄዳቸው በፊት ነው።
ቱርክ የአውሮፖ ህብረት አባል ለመሆን በመጠበቅ 50 አመታት ማስቆጠሯን እና ሁሉም የአውሮፖ የኔቶ አባላት የአውሮፖ ህብረት አባል ናቸው ብለዋል ኤርዶጋን። ፕሬዝደንቱ ቱርክ ከ50 አመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ የህብረቱ አባል እንዳትሆን ላደረጉት ሀገራት ጥሪ አስተላለፈዋል።
"ቱርክ የአውሮፖ ህብረት አባል እንድትሆን በር ክፈቱ። ለቱርክ መንገዱን ስትጠርጉ፣ እኛ ደግሞ ለፊንላንድ እንዳደረግነው ስዊድን ኔቶን እንድትቀላቀል መንገድ እንከፍታለን" ብለዋል ፕሬዝደንት ኤርዶጋን።
ቱርክ የአውሮፖ ህብረት አባል ለመሆን እጩ ብትሆንም፣ የቱርክ ዲሞክራሲ ስርአት እየተንሸራተተ ነው በሚል እና ከአውሮፖ ህብረት አባሏ ሲፕረስ ጋር ባለት ግጭት ምክንያት የአባልት ጥያቄዋ ቆሟል።
የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው እለት እንደገለጹት ቱርክ ተቃውሞዋን እንደምትተው ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ኤርዶጋን እና የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስቴር ኡልፍ ክሪስተርስን በሉታኒያው የኔቶ ስብሰባ ይገናኛሉ ተብሏል።
የፊንላድን የኔቶ አባልነት ያጸደቀችው ቱርክ፣ የስዊድን አባልነት ያልፈቀደችው በቱርክ በአሸባሪነት የተፈረጀውን የፒኬኬ ፖርቲ አባለትን አስጠልላለች በሚል ምክንያት ነበር። ቱርክ አሁን ላይ የአውሮፖ ህብረት አባልነትን እንደቅድመ ሁኔታ ይዛ መጥታለች።