የስዊድን መንግስት የቅዱስ ቁርዓን መቃጠልን የሚቃወም ህግ ሊደነግግ መሆኑ ተገለጸ
በስዊድን የኢድ አል አድሃ (አረፋ) እለት ተቃዋሚዎች ቁዱስ ቁርአን ማቃጠላቸው ቁጣን ቀስቅሷል
ከቁርዓን መቃጣል የተቆጡ የአረብ ሀገራት የስዊድን አምባሳደርን ለማብራሪያ ከመጥራት ማስጠንቀቂያ እስከ መስጠት ደርሰዋል
ጫና የበረታተበት የስዊድን መንግስት ቁርዓን ማቃጠልን በህገ ወጥነት የሚፈርጅና የሚቃወም ህግ ሊደነግግ መሆኑን አስታወቀ።
የስዊድን የፍትህ ሚኒስቴር የሀገሪቱ መንግስት ቅዱስ ቁርዓንን ማቃጠልን የሚቃወም ህግ ለመደንገግ በሂደት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
የፍትህ ሚኒስትሩ ጉናር ስትሮመር፣ ከሳምንታት በፊት በድዊድን የተፈጠረው የቅዱስ ቁርዓንን ማቃጠል እና ሌሎች መሰል ተግባራት ሀገሪቱን የጂሃዲስቶች ኢላማ ውስጥ እንድትገባ አድርጓል ብለዋል።
በስዊድን ከሽብር ተግባር ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች አሉ ያሉት ሚኒስትሩ፣ የቁርዓን መቃጠል የስዊድን የውስጥ ደህንነት ላይ ስጋትን መደቀኑንም አስታውቀዋል።
የቁርዓን ማቃጠል ክስተቶች እና እሱን ተከትሎ ከተሰጡ ፍርዶች አንጻር የህግ ሁኔታን መተንተን እንዳለብን ግልጽ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ አዲስ ህግ መደንገጉ በሂደት ላይ ነው፣ በቅርቡ መደምደሚያ ይዘን እንመለሳለን ብለዋል።
የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ከሁለት ሳምንት በፊት ሲከበር በስዊድን መዲና ስቶኮልም ተቃዋሚዎች የቅዱስ ቁርአን ማቃጠላቸው በርካታ ሀገራትን አስቆጥቷል።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኡልፍ ክሪስቴርሰን በወቅቱ በሰጡት መግለጫም፥ ቁርአን የማቃጠሉን ጉዳይ “ተገቢ አይደለም ግን ህጋዊ ነው” በሚል ማለፋቸው አይዘነጋም።
ይህንን ተከትሎም በርካታ ሀገራት ተግባሩን የተቃወሙት ሲሆን በተለይም የአረብ ሀገራት የስዊድን አምባሳደርን ለማብራሪያ ከመጥራት ማስጠንቀቂያ እስከ መስጠት ደርሰዋል።
በተለያዩ የአረብ ሀገራትም የስዊድን ባንዲራን እስከማቃጠል የደረሱ የተቃውሞ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን፣ በተለይም በኢራቅ ተቃዋሚዎች የስዊድን ኤምባሲን ሰብሮ እስከ መግባት የደረሰ ተቃውሞ አሰምተው ነበር።
ጫናው የበረታበት የስዊድን መንግሰትም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በኩል ባወጣው መግለጫ፤ በስቶኮልም መስጊድ አቅራቢያ የተፈጸመውን የቅዱስ ቅርዓን ማቃጠል ተግባር እስላም ጠል በማለት በመፈረጅ ትግባሩን ማውገዙም ይታወሳል።