ፖለቲካ
የቱርክ ፖሊስ ፕሬዚዳት ኤርዶጋን በሚገኙበት ሁነት ላይ ሊፈፀም የነበረ የቦምብ ጥቃት ማክሸፉን አስታወቀ
በፖሊስ መኪና ላይ ተጠምዶ የነበረ ቦምብ ማምከኑም ተነግሯል
በጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑንም የቱርክ ፖሊስ አስታውቋል
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሪሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን በሚገኙበት ሁነት ላይ ሊፈፀም የነበረ የቦምብ ጥቃት ማክሸፉን የሀገሪቱ ፖሊስ አስታወቀ።
ጥቃቱ በፖሊስ መኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ ሊፈፀም እንደነበረም ሲ.ጂ.ቲ.ኤን የቱርኩ አናዶሉ የዜና ኤጀንሲን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
በፖሊስ መኪና ላይ ተጠምዶ የነበረው ቦምብም ሁነቱ ወደ ተዘጋጀበት ስፍራ ከመድረሱ በፊት ተገኝቶ ኢንዲመክን መደረጉንም የቱርክ ፖሊስ አስታውቋል።
መኪናውን የሚያሽከረክረው የፖሊስ አዛዥ ከመኖሪያ ከተማው የምስራቅ ቱርኳ ኑሳይቢን ከተማ ዝግጅቱ ወደሚዘጋጅበት ሲርት ከተማ ለፀጥታ ስራ ይጓዝ እንደነበረ ተነግሯል።
ቦምቡ መምከኑን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ሪሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን በሲርት ከተማ በተዘጋጀው ሰልፍ ላይ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸውም ታውቋል።
የቱርኩ ገዢ ፓርቲ የሁነው ኤ.ኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንብር ሀምዛ ዳግ፤ በህብረተሰቡ ዘንድ መደናገጥ እንዳይፈጠር ፖሊስ ዝግጅቱ እስኪጠናቀቅ ጉዳዩን በድብቅ ይዞት መቆየቱን ተናግረዋል።
ቦምቡን ማን አጠመደው የሚለውን ለመለየት አሁን ላይ ምርመራ መካሄድ መጀመሩንም አስታውቀዋል።