ኔቶ ወደ ክሪሚያ ከተጠጋ 3ኛው የዓለም ጦርነት ይጀመራል ስትል ሩሲያ ገለጸች
ኔቶ የሰዊድን እና ፊንላንድን የአባልነት ጥያቄ ከተቀበለ ሩሲያ ወደሁለቱ ሀገራት ሚሳኤል ታቆማለች ተብሏል
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ዛሬ 124 ቀኑ ላይ ይገኛል
ኔቶ ወደ ክሪሚያ ከተጠጋ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ይጀመራል ስትል ሩሲያ ገለጸች፡፡
የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ድሚትሪ ኔድሜዴቭ እንዳሉት ኔቶ ወደ ክሪሚያ የሚያደርጋቸው እያንዳንዷ እንቅስቃሴ ሶስተኛውን የዓለም ጦርነት እንደሚያስነሳ ገልጸዋል።
ክሪሚያ የሩሲያ አንድ አካል ናት የሚሉት ኔድሜዴቭ የኔቶ ጦር ወደዚህ አካባቢ ከደረሰ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ተጀመረ ማለት ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
አሁን ላይ የሩሲያ ጸጥታ ምክር ቤት ሊቀመንበር የሆኑት ድሚትሪ ኔድሜዴቭ ኔቶ በማድሪድ ስብሰባው የፊንላንድ እና ስዊድንን ጥያቄ ከተቀበለ ሩሲያ በሁለቱ ሀገራት ድንበሮች ላይ ጥብቅ የጸጥታ ስራዎችን ከመስራት ባለፈ ኢስካንዴር ሀይፐር ሶኒክ ሚሳኤሎችን ወደ ሁለቱ ሀገራት ታጠምዳለች ብለዋል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ እየተቀዳጀችው ያለው ወታደራዊ ድል ያሰጋው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የጦሩን ቁጥር ለማሳደግ እየሰራ መሆኑ የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ዋና ጸሃፊው በቀጣይ ቀናት በማድሪድ ከሚካሄደው ስብሰባ በፊት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “የኔቶን ኃይል እናጠናክረዋለን እንዲሁም የከፍተኛ ዝግጁነት ሀይላችንን ቁጥር ከ 300 ሺህ በላይ እናሳድጋለን" ብለዋል፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ከጀመረች 124ኛ ቀኑ ላይ የደረሰ ሲሆን በነዚህ ቀናት ውስጥ አያሌ ጉዳቶች ተከስተዋል፡፡
እስካሁን ጦርነቱን ተከትሎ ከ15 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን የዓለም መግብ እና ነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ሲያሳይ ምዕራባዊያን ሀገራት ደግሞ የዋጋ ጭማሪውን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ናቸው፡፡