ሩሲያ በዩክሬን የገበያ ማዕከል ላይ የሚሳየል ጥቃት ፈጸመች ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ገለጹ
በደረሰው ጉዳት እጅጉን ያዘኑት ዜሌንስኪ “የተጎጂዎችን ቁጥር መገመት አይቻልም” ሲሉም ተደምጠዋል
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት መጠነ ሰፊ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ አስከትሏል
ሩሲያ ከ1000 በላይ ሰዎች ነበሩበት በተባለው የገበያ ማእከል የሚሳዔል ጥቃት መፈጸሟን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ አስታወቁ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከደቂቃዎች በፊት በቴሌግራም በለቀቁት ቪዲዮ ፤ የሩሲያ ኃይሎች በማእከላዊ ዩክሬኗ ክሬሜንቹክ ከተማ በሚገኝ አንድ ትልቅ የገበያ ማዕከል ላይ የሚሳዔል ጥቃት ሰንዝረዋል ብለዋል፡፡
የሩሰያ ኃይሎች የሚሳዔል ጥቃት የሰነዘሩበት ስፍራ “ለሩሲያ ጦር ምንም ዓይነት ስጋት ያልሆነ ፤ስትራቴጂያዊ ወታደራዊ ጠቀሜታ የሌለውና ሰዎች መደበኛ ኑሮአቸው የሚኖሩበት” መሆኑም ገልጸዋል፡፡
በደረሰው ጉዳት እጅጉን ያዘኑት ዜሌንስኪ “የተጎጂዎችን ቁጥር መገመት አይቻልም” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የተጋሩ የቪዲዮ በህንፃው ዙሪያ ከፍተኛ ጭስ እና የእሳት ቃጠሎ ያሳያሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፤ በስፍራው በርካታ የድንገተኛ አደጋ አገልግሎቶች የሚሰጡ አምቡላንሶች እንዲሁም በርካታ የእሳት አደጋ ተሽከርካሪወች ይታያሉ፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጀመረችውን ወታደራዊ ዘመቻ ተከትሎ ፤ በዩክሬን ምድር በርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋቱ እንዲሁም መሰረተ ልማቶች መውደማቸው አሁንም እንደቀጠሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
በዚህም በሩሲያ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃትና ግስጋሴ የተደናገጡት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ፤ የምእራባውያን ድጋፍ አልያም ደም አፋሳሽ ጦርነቱ የሚቆምበት መንገድ ካለ መፍትሄ እንዲያፈላልጉ የዓለም መሪዎችን በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
በዛሬው እለት በጀርመን ለተሰበሰቡት የቡዱን-7 መሪዎች ያቀረቡት ትያቄም ይህንኑ ነበር፡፡
ፕሬዝዳንቱ ለመሪዎቹ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት “የቡዱን 7 መሪዎች በዩክሬን ያለው ጦርነት እስከ አመቱ መጨረሻ እንዲቆም ግፊት ሊያደርጉ ይገባል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ምእራባውያን እስካሁን በሞስኮ ላይ የወሰዱት እርምጃ በቂ ነው ብለው እንደማያምኑ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ አሁንም ሀገራቱ በሩሲያ ላይ የሚጥሉትን ማዕቀብ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል፡፡