ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት “አስገድዶ መድፈርን” እንደ ወታደራዊ ስትራቴጂ ተጠቅማለች- ተመድ
ተጎጂዎቹ ባብዛኛው ሴቶች እና ልጃገረዶች ሲሆኑ ወንዶችም ጭምር ይገኙባቿል ተብሏል
ተመድ የሩሲያ ወታደሮች ድርጊት "ተጎጂዎችን ሰብዓዊ ክብር ለማዋረድ ያለመ ነው” ብሏል
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት አስገድዶ መድፈርን እንደ ወታደራዊ ስትራቴጂ ተጠቅማለች ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጸ፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ተወካይ ፕራሚላ ፓተን ለኤኤፍፒ በሰጡት ቃለ ምልልስ በዩክሬን ውስጥ በሞስኮ ሃይሎች የተፈጸሙ አስገድዶ መድፈር እና ጾታዊ ጥቃቶች የሩስያ "ወታደራዊ ስልት" እና "ተጎጂዎችን ሰብዓዊ ክብር ለማዋረድ ሆን ተብሎ የታለመ ዘዴ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዩክሬን ውስጥ አስገድዶ መድፈርን እንደ የጦር መሳሪያ ተደርጎ ጥቅም ላይ የዋለ እንደሆነ የተጠየቁት የተባበሩት መንግስታት ተወካይዋ “አዎ ሁሉም ምልክቶች አሉ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
"ሴቶች ለቀናት ታስረው ሲደፈሩ፣ ትንንሽ ወንዶችና ልጆች መድፈር ስትጀምር፣ ተከታታይ የብልት ግርዛትን ስታይ፣ ሴቶች ቪያግራ ስለታጠቀሙ የሩሲያ ወታደሮች ሲመሰክሩ ስትሰማ ይህ ወታደራዊ ስልት መሆኑ ግልጽ ነው"ም ብለዋል ተወካይዋ፡፡
ድርጊቱ ተጎጂዎችን ሰብአዊነት ለማዋረድ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፤ ሩሲያ በየካቲት ወር በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች በኋላ በዩክሬን ውስጥ “ከመቶ በላይየአስገድዶ መድፈር ወይም የወሲብ ጥቃቶች ” መፈጸማቸውን አረጋግጧል ሲሉም ነው ፓተን በመስከረም መጨረሻ ላይ የወጣውን የተመድ ሪፖርት በመጥቀስ የተናገሩት፡፡
ሪፖርቱ "የሩሲያ ኃይሎች ከአራት እስከ 82 ዓመት እድሜ ክልል በሚገኙ ዩክሬናውያን ላይ አስገድዶ መስፈርና ጾታዊ ጥቃት ፈጽሟል" የሚል ነው፡፡
ተጎጂዎቹ ባብዛኛው ሴቶች እና ልጃገረዶች ሲሆኑ ወንዶችም ጭምር ይገኙባቿል ያሉት የተመድ ተወካይዋ፤ በሰብዓዊነት ላይ ከተፈጸመው ወንጀል አንጻር ሪፖርት የተደረገው እጅግ ትንሹ ነው ብለዋል፡፡
"በተጋጋለ ጦርነት ወቅት አስተማማኝ ስታቲስቲክስ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው እናም ቁጥሩ እውነታውን በጭራሽ አያንጸባርቅም ምክንያቱም ጾታዊ ጥቃት ዝምተኛ ወንጀል ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ተመድ ይህን ይበል እንጅ የክሬምሊን ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያሉት ነገር የለም፡፡