“የኢትዮጵያ ህዝብ አንፈልግሽም ልቀቂ ካለኝ ስልጣኔን በደስታ እለቃለሁ”-ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ
አቶ ቢልልኝ መቆያ በበኩላቸው“በቶኪዮ ኦሎምፒክ ለተፈጠረው ችግር ሁለት ቦታ ይረግጡ የነበሩ አሰልጣኞች ትልቅ ድርሻ ነበራቸው” ሲሉ ተናግረዋል በመግለጫው
አትሌት ቀነኒሳ በራሱ ጊዜ በማጣሪያው ሳይሳተፍ ቀርቶ እንጂ ፌዴሬሽኑ እንዳልቀነሰውም ደራርቱ ተናግራለች
የኢትዮጵያ ህዝብ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኃላፊነት እንድቀጥል ካልፈለገ ለመልቀቅ ዝግጁ መሆኗን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ አስታወቀች፡፡
ፌዴሬሽኑ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጠ ነው፡፡
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለፕሬዝዳንቱ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ተጠይቆ የነበረው “ኃላፊነትዎን ይለቃሉ ወይ?” የሚል ጥያቄ ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉም ቀርቦ ነበር፡፡
ኮማንደር ደራርቱ ዛሬ በሰጠችው ጋዜጣዊ መግለጫ “ሕዝብ አንፈልግሽም፤ ልቀቂ ካለኝ ስልጣኔን በደስታ እለቃለሁ” ብላለች፡፡
የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ በበኩላቸው፤ “በቶኪዮ ኦሎምፒክ ለተፈጠረው ችግር ሁለት ቦታ ይረግጡ የነበሩ አሰልጣኞች ትልቅ ድርሻ ነበራቸው” ብለዋል፡፡
“ኦሎምፒክ ኮሚቴ በመክፈቻው የታየውን ጥፋት ወደ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የሚገፋው በምን መመዘኛ ነው? እኛ እንደተባለው በታክሲ ሳይሆን በተመደበልን ሰርቪስ ነው የሄድነው፤ በቦታው የደረስነውም በሰዓቱ ነበር፤ ከደረስን በኋላ በሰዓቱ እንድንገባ ማድረግ የነበረበት ራሱ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ነበር” ስትል ደራርቱ ተናግራለች፡፡
“ቀነኒሳን አልቀነስነዉም ፤ መርጠናል፤ እንዲያውም አንተ የስፖርት አባት ነህ ብትገባ ደስ ይለናል ነዉ ያልነው” ስትልም ነው ስለ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የተናገረችው፡፡
ፌዴሬሽኑ ማጣሪያዉን ሲያስብ እንደነበር የገለጸችው ፕሬዝዳንቷ መጀመሪያ የማራቶን ማጣሪያዉን ሐዋሳ ለማድረግ ታስቦ እንደነበረ ነገር ግን እንዳልተሳካ ገልጻ በመጨረሻዉ ማጣሪያ ግን ቀነኒሳ ሳይገኝ እንደቀረ ገልጻለች፡፡
የፌዴሬሽኑ እና የኦሎምፒክ ኮሚቴው ልዩነትና ሽኩቻ አጥልቶበት ነበር በተባለበት የቶኪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በአንድ የወርቅ፣ በአንድ የብር እና በሁለት የነሃስ በድምሩ በአራት ሜዳሊያዎች 56ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው፡፡