በክረምት ወራት በኢትዮጵያ የሚኖረው የዝናብ ሁኔታ ምን ይመስላል፤ አስጊነቱስ ምን ያክል ነው?
ኢጋድ ከሰኔ እስከ መስከረም ባሉት የክረምት ወራት መጠኑ ከፍ ያለ ዝናብ ስለሚኖር ጥንቃቄ እንዲደረግ መልዕክት አስተላልፏል
የኢትዮጰያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት በበኩሉ በቀጣዮቹ 10 ቀናት ከባድ ዝናብ እንደሚጠበቅ ይፋ አድርጓል
በአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ በተደጋጋሚ በሚመታው የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በመጪዎቹ ወራት ከመደበኛው መጠን ከፍ ያለ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ተነግሯል።
ማዕከላዊ እና ሰሜን ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ ፣አብዛኛው ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ በሱዳን እና በኬንያ ጠረፎች ከፍ ያለ ዝናብ ይጠበቃል ነው ያለው ቀጠናዊ ድርጅቱ።
በአንጻሩ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሰሜን ምስራቅ ደቡብ ሱዳን ከመደበኛው ከፍ ያለ ደረቅ የአየር ንብረትን ያስተናግዳሉ ብሏል ኢጋድ።
ክረምቱ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን በመሳሰሉ ሀገራት ቀደም ብሎ መታየት ሲጀምር። በጅቡቲ እንዲሁም በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን ዘግየት ብሎ እንደሚጀምር ኢጋድ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።
የኢትዮጰያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ትናንት ይፋ ባደረገው መረጃ ደግሞ በቀጣዮቹ አሥር ቀናት ሰፊ ቦታዎችን ያካተተና የተጠናከረ ዝናብ እንደሚኖር አመላክቷል
በዚህም በአጠቃላይ በሚቀጥሉት ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ጅማ፣ ኢሉባቦር፣ ቦረና እና ምስራቅ ቦረና፤ ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ፣ ባሌ ከመደበኛው ከፍለ ያለ ዝናብ እንደሚጠበቅ አስታውቋል።
እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜን፣ ማዕከላዊ፣ ደቡብ እና ምዕራብ ጎንደር፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ጎጃም እና አዊ ዞኖችን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች ላይ ከፍ ያለ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖራቸው ነው ይፋ ያደረገው።