አይኤምኤፍ የዓለምን የኢኮኖሚ ድቀት ለማስቀረት “የተቀናጀ የፖሊሲ እርማጃ መውሰድ” አስፈላጊ ነው ሲል አሳሰበ
ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ፤ አፋጣኝ ተግዳሮቶችን በመፍታት የዓለም ኢኮኖሚን ማረጋጋት ወሳኝ መሆኑ ተናግረዋል
የዓለም ንግድ ድርጅት በቅረቡ ዓለም ወደ “ዓለም አቀፋዊ ውድቀት” እየተንደረደረች ነው ብሎ ነበር
የዓለም የገንዘብ ድርጅት ኃላፊ ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ በዓለማችን እየከፋ የመጣውን የኢኮኖሚ ድቀት ለማስቀረት የተቀናጀ የፖሊሲ እርማጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው ሲሉ አሳሰቡ፡፡
የዋጋ ግሽበትን መዋጋትን ጨምሮ “አፋጣኝ ተግዳሮቶችን በመፍታት የዓለም ኢኮኖሚን ማረጋጋት ወሳኝ ነው” ያሉት ጆርጂዬቫ ፤ ለዚህም የፖሊሲ አውጪዎች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ሂደቱ አሰልቺ ሊሆን ቢችልም ለመፍትሄው መስራቱ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ማለታቸውም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደ አይኤምኤፍ ኃላፊዋ ሁሉ የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ በበኩላቸው ዓለም ወደ “ዓለም አቀፋዊ ውድቀት” እየተንደረደረ ነው ሲሉ በመቅረቡ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም፡፡
በዩክሬን ያለው የሩሲያ ጦርነት፣ የአየር ንብረት ቀውስ፣ የምግብ ዋጋ እና የኢነርጂ ድንጋጤ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መዘዝ ለዓለም የኢኮኖሚ ውድቀት ሁኔታዎችን እየፈጠሩ ናቸው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ እድገትን ለማነቃቃት ስር ነቀል ፖሊሲዎች ተግባራዊ መደረግ አለባቸው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ በጄኔቫ በተሳለተው ዓለም አቀፉ የንግድ ፎረም መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር “ወደ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ድቀት እየገባን ያለ ይመስለኛል፤ እናም በተመሳሳይ ጊዜ ስለ ማገገም ማሰብ መጀመር አለብን ፤እድገትን መመለስ አለብን” ብለዋል፡፡
የንግድ ትንበያ ቁጥሮች የሚያመላክቱት ነገሮች ጥሩ እንዳመይሆሆንም ነበር የገለጹት ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ፡፡
ክለውም “የደህንነት ፣ የአየር ንብረት፣ የኢነርጂ ፣ የምግብ ዋጋ መናር ስጋቶች አሉብን ፣ስለዚህም እነዚህ ሁሉ ችግሮች ባሉበት እንደተለመደው ቢዝነስ ለመስራት አንችልም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የቀድሞ የናይጄሪያ ፋይናንስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ “ማዕከላዊ ባንኮች የወለድ ምጣኔን ከማጥበቅ እና ከመጨመር በስተቀር ብዙ ምርጫ የላቸውም - ነገር ግን በታዳጊ ገበያዎች እና በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ላይ የሚያስከትሉት መዘዞች በጣም ከባድ ናቸው ምክንያቱም እነሱም የወለድ ምጣኔን ይጨምራሉ”ማለታቸውም ነበር ኤኤፍፒ የዘገበው፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ፤ ማዕከላዊ ባንኮች የዋጋ ግሽበት በጠንካራ ፍላጎት ወይም የዋጋ ንረቱ በአቅርቦት በኩል ካለው መዋቅራዊ ችግር ጋር የተያያዘ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ኦኮንጆ-ኢዌላ፤ ዋነኛ ትኩረታቸው የምግብ ዋስትናን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል እና ከዚያም የኃይል አቅርቦትን ማረጋገጥ መሆኑም ገልጸዋል፡፡
“የሚያስጨንቀኝ በቂ ምግብ ካለማግኘት ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው” ሲሉም ነበር የተደመጡት የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተሯ ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ፡፡