ጀርመን በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ለገጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ ማረጋጊያ 65 ቢሊየን ዩሮ መደበች
በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከፍተኛ ጉዳትን ካስተናገዱ የአውሮፓ ሀገራት መካከል ጀርመን ዋነኛዋ ናት
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ከገቡ 193ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል
ጀርመን በጦርነት ምክንያት ለገጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ ማረጋጊያ 65 ቢሊየን ዩሮ መደበች።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ስድስት ወራት ያለፉት ሲሆን ጦርነቱ በዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዲመዘገብ ምክንያት ሆኗል።
ይህ በዚህ እንዳለም ጦርነቱ በዓለም ዲፕሎማሲ ላይ የተለያዩ መፋለሶችን ያስከተለ ሲሆን ሀገራት ከትብብር ይልቅ ጎራ ለይተው እንዲሰለፉ እያደረገም ይገኛል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ላይ በተለያየ መንገድ በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ በሩሲያ ላይ ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦችን ጥለዋል።
ሩሲያም የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ስትሆን ማዕቀቡ ለአውሮፓ ሀገራት የምታቀርበውን ጋዝ ሽያጭ እክል አስከትሏል።
ይሄንን ተከትሎም 40 በመቶ ለሚሆኑ የአውሮፓ ሀገራት ነዳጅ ስታቀርብ የነበረችው ሩሲያ በማዕቀቡ ምክንያት ለአውሮፓውያን ነዳጅ መላክ አለመቻሏን በተደጋጋሚ ገልጻለች።
በነዳጅ ዕጥረት እየተፈተነ ያለው የአውሮፓ ህብረትም በሩሲያ ላይ የጣለውን ማእቀብ እስከማላላት ቢደርስም ሞስኮ ነዳጇን በሚፈለገው ልክ አለመላኳን ሮይተርስ ዘግቧል።
የአውሮፓ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑት ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ፣ ቤልጂየም እና ሌሎች ሀገራት በነዳጅ ዕጥረት እየተፈተኑ ናቸው ተብሏል።
እነዚህ ሀገራት ሩሲያ ነዳጇን እንደጦር መሳሪያ እየተጠቀመችበት ነው ሲሉም ሙሉ ለሙሉ ወደ አውሮፓ ነዳጅ መላክ ያቆመችው ሞስኮን ከሰዋል።
በነዳጅ እጥረት ሳቢያም የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ዜጎች የደመወዝ ጭማሪን ጨምሮ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲደረግላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው።
የጀርመን መንግስትም በነዳጅ እጥረት የተጎዳውን የበርሊን ኢኮኖሚው ለማረጋጋት 65 ቢሊዮን ዩሮ መመደቡን ገልጿል።
በጀቱ ለዜጎች ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት ከማቅረብ ጨምሮ የነዳጅ ድጎማ እና የግብር እፎይታዎች እንደሚደረጉ የሀገሪቱ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ተናግረዋል።