አይኤምኤፍ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት አዝጋሚ እድገት እንደሚያስመዘግቡ ተነበየ
አይኤምኤፍ ሀገራቱ በዚህ አመት 3.4 በመቶ እድገት ያስመዘግባሉ ብሏል
አይኤምኤፍ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ከ32 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በአስከፊ ድህነት ውስጥ እንደሚገኙ ገልጿል
ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ከዓለማችን ቀርፋፋ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚያስመዘግቡ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ተነበየ፡፡
ሀገራቱ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገት የሚያስመዘግቡት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ነው ተብሏል።ከሰሃራ በረሃ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በያዝነው ዓመት የ3. 4 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘግባሉ ተብሏል።
ይህም አካባቢው ከዓለማችን ሀገራት ዝቅተኛ ኢኮኖሚያዊ አድገት አንደሚያስመዘግቡ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) በድረገጹ አስታውቋል።
ከሰሀራ በታች ያሉ አገራት ባሳለፍነው ዓመት 1.9 በመቶ እድገት ማስመዝገባቸው ይታወሳል።ሀገራቱ በያዝነው ዓመትም የኮሮና ቫይረስ ጉዳት መሻሻል ባለማሳየቱ እድገቱ ካሳለፍነው ዓመት አንጻር መሻሻል ቢያሳይም የሚያስመዘግቡት እድገት አጥጋቢ እንደማይሆን ድርጅቱ ገልጿል።
ከ32 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን የያዘው ይህ አካባቢ የበለጸጉ ሀገራት የኮሮና ቫይረስ ተጽዕኖዎችን መከላከል የሚያስችሉ ድጋፎችን እንዲያደርጉ ድርጅቱ ጥሪ አቅርቧል።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በርካታ ዜጎች ስራቸውን አጥተዋል ያለው ድርጅቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታ ሊውሉ የነበሩ በጀቶች ታጥፈው ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ ስራዎች እየዋሉ በመሆኑ ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁሟል።
ኬንያ ቦትስዋና ኒጀር ሞሪሺየስ እና ዩጋንዳ በአንጻራዊነት በያዝነው ዓመት የተሻለ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደሚያስመዘግቡ የድርጅቱ ትንበያ ያስረዳል።
የአፍሪካ ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤቶቹ ናይጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ከ2.5 አስከ 3.1 በመቶ እድገት ያስመዘግባሉም ተብሏል።
በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምየአፍሪካ ዳይሬክተር አቶ አበበ አዕምሮ እንዳሉት ከሰሀራ በታች ላሉ ሀገራት የኢኮኖሚ መቀዘቀዝ ኮሮና ቫይረስ ዋነኛው ቢሆንም የፖለቲካ አለመረጋጋት የውጭ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ መቀዛቀዝ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።