ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት እስከ 3.4 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘግባሉ- ዓለም ባንክ
ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚ እጥፍ በሆነ ፍጥነት ያድጋል- ባንኩ
ሀገራቱ ለዜጎቻቸው የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት መስጠት መጀመራቸው ለኢኮኖሚው ማገገም የበኩሉን ድርሻ አለው
በአውሮፓውያኑ 2021 ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት የከ2 ነጥብ 3 እስከ 3 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚያስመዘግቡ የዓለም ባንክ አስታወቀ።
ለኢኮኖሚ እድገቱ ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስራ ላይ ባዋሉት የኢኮኖሚ ፖሊስ ማሻሻያዎች ላይ በመመርኮዝ እንደሚመዘገብም ባንኩ በትንበያው አስታውቋል።
ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ልክ እንደሌሎች የዓለም ሀገራት በ2020 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ጥለው የቆዩ መሆኑን በማስታወስ፤ ይህም እንደ ንግድ እና ቱሪዝም ያሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን መጉዳቱን አስታውሷል።
አሁን ላይ ግኝቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ ግን ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚ እጥፍ በሆነ ፍጥነት እንደሚያገግም ባንኩ በትንበያው አስታውቋል።
በተለይም ሀገራቱ ዜጎቻቸውን ለመከተብ እያሳዩት ያለው ጥረት ለኢኮኖሚ እድገቱ ማገገም የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም ባንኩ በትንበያው አመላክቷል።
ቅይጥ ኢኮኖሚ ያላቸው እንደ ኬንያ እና ኮት ዲቯር እንዲሁም በማዕድን ላይ ጥገኛ የሆነ ኢኮኖሚ ያላቸው እንደ ቦትስዋና እና ጊኒ ያሉ ሀገራት ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያድግ አና ኢንቨስትመንትን የመሳብ አቅማቸው እንደሚጨምርም ባንኩ በተንበያው አስታውቋል።
ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ከፍተኛ ኢኮኖሚ ያላቸው ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና አንጎላ ደግሞ በ2021 ወደ ኢኮኖሚ እድገት እንደሚመለሱም ትንበያው አመላክቷል።