አይ.ኤም.ኤፍ በኮሮና ለተጎዳው የአፍሪካ ኢኮኖሚ “ጠንካራ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ያስፈልጋል” አለ
አይ.ኤም.ኤፍ በኮቪድ-19 ምክንያት እጅግ የከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ መፈጠሩንና ሚሊዮኖች በድህነት ተዘፍቀዋልም ብሏል
አፍሪካ በቀጣይ በዲጂታል ቴክኖሎጂዎችና አየር ንብረትን መቋቋም በሚችሉ መሠረተ ልማቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንዳለባትም ተጠቁሟል
አፍሪካ ከ ኮቪድ-19 ቀውስ በማገገም ወደ ተጠናከረ የእድገት ጎዳና እንድትመለስ የተጠኑና የተስተካከሉ የሀገር ውስጥ ፖሊሲዎች እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጠንካራ ድጋፍ ያስፈልጋታል ሲሉ የአይ.ኤም.ኤፍ እና የአፍሪካ ካውከስ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡
የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት /አይ.ኤም.ኤፍ/ ማኔጂንግ ደይሬክትር ክርስቲና ጂዮርጄቫ እንዲሁም የአፍሪካ ካውከስ ኃላፊው ዶምቴን ንዲሆኩብዎዮ፤ የ12 የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ ተወካዮችን ካካተተው የአፍሪካ አማካሪ ቡድን ጋር ምክክር ያደረጉ ሲሆን በአፍሪካ ጉዳይ ላይ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ኃላፊዎቹ “የ ኮቪድ-19 የክትባት ማምረቻ አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንዲሁም የክትባት ተደራሽነትን ማስፋት ቁልፍና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተግባራት ናቸው” ብልዋል በመግለጫቸው፡፡ ተጋላጭ ቡድኖችን ለማገዝ የሚረዱ ፖሊሲዎችን የመቅረፅ ተግባር በዛው ልክ አስፈላጊ እንደሆነም ጭምር ማነሳታቸውንም ነው ሮይተርስ የዘገበው፡፡
አፍሪካ በኮቪድ-19 የጤና ድንገተኛ ሁኔታ ተጠምዳለች፤ እናም ይህ በአህጉሪቱ ምናልባትም ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ያልታየ እጅግ የከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲፈጠርና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በድህነት ውስጥ እንዲዘፈቁ ምክንያት እንደሆነም አስረድተዋል ኃላፊዎቹ፡፡
ምንም እንኳ በነዳጅ የበለፀገውን የአህጉሪቱ ሰሜን አፍሪካ ክፍል በፍጥነት ያድጋል ተብሎ ቢጠበቅም፤ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የመልሶ ማገገም ሂደቱ በጣም ቀርፋፋ እንደሆነ ነው የአይ.ኤም.ኤፍ እና የአፍሪካ ካውከስ መሪዎች የሚናገሩት፡፡ በብዙ ሀገራት የነፍስ ወከፍ ገቢ እ.ኤ.አ. ከ2025 በፊት ወደ ቀውስ ደረጃ ይመለሳል ተብሎ እንዳልተጠበቀም ጭምር ፡፡
ኃላፋቹ የተጋረጠውን ችግር ለመፍታት በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እና አየር ንብረትን መቋቋም በሚችሉ መሠረተ ልማቶች ላይ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ማፍሰስ እንዲሁም የትራንስፎርሜሽን ፖሊሲዎችን መንደፍ አስፈላጊ ነው ሲሉ ምክር ሀሳብ አቅርበዋል፡፡