የኬንያ የዕዳ ጫና ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ መሸጋገሩን አይ.ኤም.ኤፍ አስታወቀ
አይ.ኤም.ኤፍ ለኬኒያ 739 ሚሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ ፈንድ አጽድቋል
በ2019 መጨረሻ የኬንያ እዳ ከጥቅል ሀገራዊ ምርቷ 61.7 በመቶ ያህል ይሸፍናል
በ2019 መጨረሻ የኬንያ እዳ ከጥቅል ሀገራዊ ምርቷ 61.7 በመቶ ያህል ይሸፍናል
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዛሬ ባወጣው የጥናት ሪፖርት እንዳስታወቀው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የኬንያ የዕዳ ጫና መካከለኛ ደረጃ ላይ ከነበረበት ወደ ከፍተኛ ተሸጋግሯል፡፡
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ቀመር በ2019 መጨረሻ፣ የምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር እዳ ከጥቅል ሀገራዊ ምርቷ (GDP) 61.7 በመቶ ያህል የሚሆነውን ይሸፍናል፡፡ ይሄም በ2015 ከነበረው 50.2 በመቶ ጋር ሲነጻጸር በ 4 ዓመታት ውስጥ የ11.5 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ነው፡፡
የሀገሪቱ የእዳ ጫና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው፣ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተጨማሪ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አዲስ የባቡር መስመር ግንባታን ጨምሮ በሀገሪቱ በተጀመሩ ትልልቅ የመሰረተልማት ፕሮጄክቶች ግንባታ ምክንያት በተፈጠረ የበጀት ጉድለት ነው ተብሏል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ደግሞ የሀገሪቱን የዕዳ ቀውስ ይበልጥ እንደሚያባብስም ነው የተገለጸው፡፡
የዕዳ ጫና ችግሩን ለመቅረፍ የኬንያ መንግስት የተጨማሪ እሴት ታክስ እና የገቢ ግብር ቅነሳን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን ቢወስድም፣ ይህ ሌሎች መለኪያዎች ላይ የባሰ ችግር መፍጠሩን አይ.ኤም.ኤፍ ገልጿል፡፡ ባለፈው ሳምንት ድርጅቱ ለኮሮና ቫይረስ መከላከል የሚውል 739 ሚሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ ፈንድ ለኬኒያ አጽድቋል፡፡
ምንጭ፡- ሲጂቲኤን