ኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከጃክ ማ የተበረከቱ የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ሱዳን ላከች
ኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከጃክ ማ የተበረከቱ የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ሱዳን ላከች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ቻይናዊው ባለሃብት ጃክ ማ በጋራ በወሰዱት ኢኒሺዬቲቭ አማካኝነት የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ወረርሽኝን በአፍሪካ ለመከላከል የሚያግዙ የሕክምና መርጃ ቁሳቁሶች የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ ትናንት ምሽት ከአዲስ አበባ ሱዳን ካርቱም ደርሷል።
የሕክምና መገልገያ ድጋፉን የያዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እቃ ጫኝ አውሮፕላን በካርቱም አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በሱዳን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ለሱዳን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር አክራም አቶም የሕክምና መገልገያዎቹን አስረክበዋል።
ሚኒስትሩ በርክክቡ ወቅት ቫይረሱን ለመከላከል ከፍተኛ ርብርብ በሚጠይቅበት በዚህ ወሳኝ ሰዐት ሱዳን የድጋፉ የመጀመሪያ መዳረሻ በመሆኗ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በተደረገው ድጋፍ ለኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሱዳን መንግስትና ሕዝብ ስም የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።
አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ በበኩላቸው ይህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተወሰደው ኢኒሺዬቲቭ የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ወንድም ለሆነው የሱዳን ሕዝብና ለሌሎች የአፍሪካ ሕዝቦች አንገብጋቢ ጉዳዮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እና መፍትሔ በማፈላለግ ረገድ ያለውን ቁርጠኘነት በድጋሚ ያረጋገጠበት አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሕክምና መገልገያ ድጋፉ በቀጣይ ለግብጽ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚከፋፈል መሆኑን ጠቁመው የሎጂስቲክና የሥርጭት ሥራው ሙሉ በሙሉ የአፍሪካውያን ኩራት በሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በነጻ የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።
ለሱዳን የተላከው የሕክምና መገልገያዎች ድጋፍ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ኪቶች፣ የአፍ መሸፈኛ ጭምብሎች እና የሕክምና ባለሙያዎች ከቫይረሱ ጋር ንክኪ እንዳይኖራቸው የሚከላከሉ ልብሶችን ያካተተ ነው።
የድጋፍ ቁሳቁሶቹ ወደ ጅቡቲ፣ ኤርትራ እና ግብጽም ተልከዋል፡፡
ምንጭ፡-በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ