የአውሮፓ ኩባንያዎች የሩሲያን ጋዝ በሩብል ለመግዛት የባንክ ሂሳብ ከፈቱ
ፑቲን ሩሲያ ወዳጅ ላልሆኑ ሀገራት ነዳጅ የምትሸጠው በራሷ የመገበያያ ገንዘብ ብቻ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል
በሩሲያ ባንክ ሂሳብ ከከፈቱ ኩባንያዎች መካከል የጀርመን ጋዝ ኩባንያ ይገኝበታል ተብሏል
የአውሮፓ ኩባንያዎች ጋዝ ለመግዛት በሩሲያው ጋዝፕሮም ባንክ ሂሳብ መክፈታቸው ተገለጸ፡፡
ኩባንያዎቹ የባንክ ሂሳብ የከፈቱት ሩሲያ ወዳጅ ያልሆኑ ብላ የፈረጀቻቸው ሀገራት የጋዝ ምርቷን በራሷ የመገበያያ ገንዘብ እንዲገዙ በጠየቀችው መሰረት ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን መጋቢት 31 ቀን 2022 ወዳጅ ያልሆኑ ሀገራት የሩሲያን ጋዝ መግዛት ያለባቸው በሩብል መሆን አለበት የሚል መመሪያ ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡
ይህንን ተከትሎም አሁን ላይ የአውሮፓ ኩባንያዎች ጋዝ ለመግዛት ጋዝፕሮም ባንክ ጄኤስ ሲ በተባለ የሩሲያን ባንክ ሂሳብ መክፈታቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡ በጥቅሉ 20 የሚሆኑ የአውሮፓ ኩባንያዎችም በጋዝፕሮም ሂሳብ መክፈታቸው ተሰምቷል፡፡
በብሉምበርግ ዘገባ ላይ በሩሲያ ባንክ ሂሳብ ሊከፍቱ የተዘጋጁትን ኩባንያዎች ቁጥር እንጅ የኩባንያዎቹ ማንነት አልተጠቀሰም፡፡
የአውሮፓ ጋዝ ገዥዎች ቭላድሚር ፑቲን ያስተላለፉትን ትዕዛዝ እንዴት ተግባራዊ ይደረግ ለማለት ለሳምንታት ዘለቀ ውዝግብ ውስጥ ገብተው እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡
ጋዝ የሚገዙ ኩባንያዎች አንድ የባንክ ሂሳብ በውጭ ምንዛሬ ሌላ ደግሞ በሩሲያ መገበያያ ገንዘብ ሩብል በድምሩ ሁለት የባንክ ሂሳብ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጾ ነበር፡፡
ፖላንድ እና ቡልጋሪያ ይህንን ቅድመ ሁኔታ ውድቅ ካደረጉ በኋም ባንኩ ጋዝ ወደ ሀገራቱ መላኩን አቁሟል፡፡
የጀርመን የጋዝ ኩባንያ በሩሲያ ባንክ ሂሳብ መክፈቱም ተገልጿል፡፡ አሁን ባለው አካሄድ ፑቲን ተግባራዊ ያደረጉት መመሪያ መተግበር ጀምሯል ነው የተባለው፡፡