የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ኢትዮጵያውያንን ያፈራው አንጋፋው ጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት
ትምህርት ቤቱ የእንግሊዙ “ጄነራል ዊንጌት ለኢትዮጵያ ነጻነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ” መታሰቢያ በሚል የተመሰረተ ነው
ጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት በ1938 ዓ.ም ነው 38 ተማሪዎች ተቀብሎ የመማር ማስተማር ስራውን የጀመረው
የ75 ዓመት እድሜ ባለጸጋው ጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት አንጋፋ ከሚባሉ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው።
ትምህርት ቤቱ ጣልያን ለ2ኛ ጊዜ ኢትዮጵያን ሲወር የእንግሊዙ ጄነራል ኦርድ ቻርለስ ዊንጌት የኢትዮጵያን ጦር በመምራት “ወራሪው የጣልያን ጦር ከኢትዮጵያ እንዲወገድ ላደረጉት አስተዋጽኦ” መታሰቢያ በሚል በአጼ ኃይለስላሴ እንደተመሰረተ ታሪክ ያመላክታል።
የጄነራል ዊንጌት የቀለም ትምህርት ቤት በወቅቱ ከየክፍለ ሀገሩ ከፍተኛ የ8ኛ ክፍል ውጤት ያመጡትን ተማሪዎች ተቀብሎም ነበር የመማር ማስተማር ሂደቱ የጀመረው።
አሁኑ ጄነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በ1938 ዓ.ም ነበር 38 ተማሪዎች ተቀብሎ በአዳሪ ትምህርት ቤትነት ስራ የጀመረው ከአል-ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ እንዳደረጉት እንደ ትምህርት ቤቱ ምክትል አካዳሚክ ዲን አቶ አድማሱ በቀለ ገለጻ፡፡
የደርግ መንግስት የሀገሪቱን በትረ ስልጣን መጨበጡን ተከትሎም፤ ትምህርት ቤቱ በ1975 ዓ.ም ስሙ ወደ “ጀነራል ዊንጌት የኮንስትራክሽን ትምህርት ቤት” ተቀይሮ በተለያዩ ዘርፎች ስልጠናዎች ሲሰጥ ቆይቷል።
በመቀጠል በ1994 በኢህአዴግ መንግስት አዲስ የትምህርት ፖሊሲ መሰረት ትምህርት ቤቱ በተለያዩ ደረጃዎች የቴክኒክ ሙያና ስልጠናዎች መስጠት እንደጀመረም ምክትል ዲኑ አንስተዋል።
“ትምህርት ቤቱ በ2005 የጄነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሚል ስያሜ አግኝቶ፤ አሁን ላይ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 5 ስልጠናዎች እየሰጠ ነው”ም ብለዋል አቶ አድማሱ፡፡
የጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት በርካታ አንጋፋ ፖለቲከኞች፣ ሳይንቲስቶች፣ ጋዜጠኞች እና ባለሙያዎችን አፍርቷል።
አቶ አድማሱ “የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ኢንጂነር ያየህ ይራድ ቅጣው እንዲሁም የኦነግ መሪው ኦቦ ዳውድ ኢብሳ ጄነራል ዊንጌት ካፈራቸው አንጋፋ ሰዎች ናቸው” ሲሉም በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጁ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ቅርንጫፍ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡
እንደ አቶ አድማሱ ገለጻ ኮሌጁ በ2017 ዓ.ም ሁለተኛው የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ የመሆን ራዕይን ሰንቆ እየሰራ ነው።
ጄነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በአፍሪካ ተወዳዳሪ የትምህርት ተቋም ለመሆን በቅርቡ ለዓለም ባንክ ፕሮፖዛል አቅርቦ 14 ነጥብ 85 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በማግኘት ስራዎች መጀመሩንም ገልጸዋል።