በኢትዮጵያ በኮሮና ተይዘው ወደ ህክምና ማዕከላት ከሚገቡት 100 ሰዎች መካከል 83ቱ ኦክስጅን ይፈልጋሉ ተባለ
ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከ250 ሺህ ማለፉን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል
በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ከሚገኙ 987 ታማሚዎች መካከል 110ሩ ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ ላይ የሚገኙ ናቸው
በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ቫይረስ መገኘቱ ከተረጋገጠ እለት ጀምሮ እስከ ትናንት ሚያዝያ 16 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ 250 ሺ 955 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው በምርመራ መረጋገጡን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ እስካሁን በአጠቃላይ ለ2 ሚሊዬን 544 ሺ 95 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ለመለየት የሚያስችል የላብራቶሪ ምርመራ መደረጉን አስታውቋል፡፡
ቫይረሱ ከተመረመሩት ከእነዚህ ሰዎች መካከል በ250 ሺ 955 ላይ መገኘቱንም ነው የገለጸው፡፡
57‚409 ሰዎች በአሁኑ ሰዓት በቫይረሱ ተይዘው ይገኛሉ፡፡
190‚013 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን 3‚531 ታማሚዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል ፡፡
እስከ ትናንት ድረስ ባለው መረጃ 987 ታማሚዎች በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ከእነዚህም ውስጥ 110 ግለሰቦች ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡
ወደ ኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ከሚገቡት 100 ግለሰቦች 83 የሚሆኑት በተለያየ መጠን ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡
በመሆኑም እያንዳንዱ ሰው ማስክ ማድረግ፣አዘውትሮ እጅን በሳሙና እና በውሃ በመታጠብ ወይም በሳኒታይዘር በማፅዳት እና አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ራሱን እና ቤተሰቡን እንዲሁም ማህበረሰቡን ከበሽታው እንዲጠብቅ ኢንስቲትዩቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአንድ ወር ውስጥ ከግማሽ ሚሊዬን በላይ ሰዎች የቫይረሱን ክትባት አግኝተዋል መባሉ የሚታወስ ነው፡፡