“የኮሮና ወረርሽኝ የኤች አይ ቪ ምርመራዎች በ41 በመቶ እንዲቀንሱ አድርጓል”- ጥናት
የወባ ምርመራ በ31 በመቶ እንዲሁም የድህረ ወሊድ ክትትል በ43 በመቶ መቀነሱንም ነው ጥናታዊ ሪፖርቱ ይፋ ያደረገው
ጥናቱ በወረርሽኙ ምክንያት የሳንባ ሪፈራል በ59 በመቶ መቀነሱንም አመልክቷል
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአፍሪካ እና እስያ ያለውን የኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ የሳንባ እና የወባ ህክምና አገልግሎቶችን ክፉኛ ማዛባቱንአዲሱ የግሎባል ፈንድ ጥናታዊ ሪፖርት አመለከተ፡፡
ሪፖርቱ በህክምና መሰረተ ልማት ተቋማት ላይ አስቸኳይ የማሻሻያዎች እርምጃዎችን በመውሰድ አገልግሎቱን መታደግ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡
ፈንዱ ከባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወዲህ እስከ መስከረም ባሉት 6 ወራት በአፍሪካ እና እስያ 32 ሃገራት በሚገኙ 506 የጤና ተቋማት ወረርሽኙ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የደቀነውን ችግር ለመለየት የሚያስችል ቅኝት ማድረጉን አስታውቋል፡፡
በቅኝቱ የኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ የሳንባ እና የወባ ተጠቂዎችንና ሟቾችን ቁጥር ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ አሳሳቢ ሁኔታዎችን መመልከቱን ነው ያስታወቀው፡፡
የኤች አይ ቪ ምርመራ በ41 በመቶ፣ የሳንባ ሪፈራል በ59 በመቶ፣ የወባ ምርመራ በ31 በመቶ እንዲሁም የድህረ ወሊድ ክትትል በ43 በመቶ መቀነሱንም በጥናታዊ ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡
የኮሮና ቫይረስን ለመመርመርና ለማከም የሚያስችሉ ህክምና ግብዓቶች እጥረት እንዳጋጠመም ጠቁሟል፡፡
አንዳንድ የጤና ተቋማት መድሃኒቶችን ለታካሚዎቻቸው ቀደመው በመስጠት ጭምር የወረርሽኙን ጫና ለመቋቋም ጥረት ስለማድረጋቸውም ነው ሪፖርቱ የሚያወሳው፡፡
ግሎባል ፈንድ COVID-19 ን ለመዋጋት እና ከ 100 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ በኤች አይ ቪ፣ በቲቢ እና በወባ ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ ለማቃለል ቀድሞውኑ ወደ 1 ቢሊዮን የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር በመመደብ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ነው የገለጸው፡፡
አሁንም ድጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል ተጨማሪ 10 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብሏል፡፡
ፈንዱ እስከ እኤአ 2021 ድረስ ሊገለገል የሚችልበትን 3.7 ቢሊዮን ዶላር እንዳሰባሰበም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡