የዩክሬን ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ አካባቢ በ"ኃይለኛ ፍንዳታ"መናወጡን የዓለም የአቶሚክ ተቆጣጣሪ አካል አስታወቀ
ዛፖሪዝሂያ በአውሮፓ ትልቁና በዓለም ላይ ካሉት 10 ትላልቅ የኒውክሌር ኃይል ጣቢያዎች መካከል አንዱ ነው
የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ "ዜናው ... እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው” ብለዋል
የዩክሬን ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ አካባቢ በ"ኃይለኛ ፍንዳታ" መናወጡ የዓለም የአቶሚክ ተቆጣጣሪ አካል አስታወቀ፡፡
የተመድ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ በሩሲያ ኃይሎች ስር በሚገኘው ዛፖሪዝዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ ትላንትና ማምሻውን እና ዛሬ ማለዳ ላይ "ኃይለኛ ፍንዳታዎች" ተከስተዋል ብለዋል፡፡
ፍንዳታዎቹ በአውሮፓ ትልቁ የኒውክሌር ጣቢያ ላይ እንደ አዲስ ያገረሸ " የተኩስ ልውውጥ" ስለመኖሩ አመላካች ናቸው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ሁኔታው እጅግ እንደሚያስባቸው ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
"ዜናው ... እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው፤ በዚህ ዋና የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ ፍንዳታዎች ተከስተዋል፤ ይህም ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌለው ነው "ሲሉም ነው ግሮሲ በጽሑፍ ባወጡት መግለጫ የጉዳዩን አሳሳቢነት የገለጹት፡፡
"ከዚህ በስተጀርባ ያለው ማንኛውም አካል ከድርጊቱ መቆጠብ አለበት፤ ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ እንዳልኩት፣ በእሳት እየተጫወተ ነው!” ሲሉም አክለዋል፡፡
ዋና ዳይሬክሩር ሁለቱም በጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሩሲያ እና ዩክሬን በዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ ዙሪያ ያለውን አጠቃላይ የደህንነት እንዲጠብቁም በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡
ግሮሲ የኒውክሌር ጣቢያው አከባቢ ደህንነት በዘለቂነት ለማረጋገጥ ከሁለቱም ወገኖች ጋር ከፍተኛ ምክክር ቢያደረጉም አስካሁን ባለው ሁኔታ አጥጋቢ የሚባል ውጤት አለመታየቱ ይነገራል፡፡
"የዚህ አከባቢ ደህንነት እውን እስኪሆን ድረስ ተስፋ አልቆርጥም” ም ነው ያሉት ግሮሲ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩስያ በዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ለተከሰተው ፍንዳታ ኪቭን ተጠያቂ አድርጋለች፡፡
ኪቭ "በዛፖሪዝሂሂያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ በሰው ሰራሽ አደጋ ስጋት ለመፍጠር ያሰበችውን ቀውስ እንደቀጠለችበት ነው"ም ብላለች ሩሲያ ባወጣችው መግለጫ፡፡
ዩክሬን ደረሰ ስለተባለው ፍንዳታ እስካሁን ያለችው ነገር የለም፡፡
በደቡብ ምስራቅ ዩክሬን የሚገኘው ዛፖሪዝሂያ አቶሚክ ሃይል ማመንጫ በአውሮፓ ትልቁና በዓለም ላይ ካሉት 10 ትላልቅ የኒውክሌር ኃይል ጣቢያዎች መካከል አንዱ ነው።
እናም በጦርነት ውስጥ የሚገኙትና እርስ በርስ የሚካሰሲት ሩሲያና ዩክሬን በጣቢያው ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከሀገራቱ በዘለለ ለተቀረው ዓለም ያልተፈለገ መዘዝ ይዞ እንዳይመጣ ተሰግቷል።