የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርነትን የዲ.አር.ኮንጎ ፕሬዝደንት ከደቡብ አፍሪካ አቻቸው ተረከቡ
መሪዎች በአካል ያልተገናኑበት የሕብረቱ ስብሰባ አጀንዳዎች ምንድን ናቸው?
34ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በበይነ መረብ እየተካሔደ ነው
በየዓመቱ ጥር መጨረሻና የካቲት መጀመሪያ የሚካደው የአፍሪካ ሕብረት መደበኛ ስብሰባ በዚህ ዓመት በተለየ መልኩ መካሄድ ጀምሯል፡፡ 34ኛው የመሪዎች ጉባዔ እንደወትሮው ሁሉ መሪዎችን በአካል ባያገናኝም የውይይት አጀንዳዎችን በመምረጥ በበይነ መረብ እየተካሄደ ነው፡፡
የአፍሪካ ሕብረት የአስፈጻሚዎች ስብሰባ ከሰሞኑ የተካሄደ ሲሆን የመሪዎቹ ጉባዔ ዛሬ ጀምሯል፡፡ በዚህም መሰረት የመሪዎቹ ጉባዔ ዛሬና ነገ ይካሄዳል፡፡
የሕብረቱ መሪዎች ስብሰባውን በአካል ያላደረጉበት ምክንያት የኮሮና ቫይረስ ሲሆን ወረርሽኙም አንዱ የጉባዔው አጀንዳ ነው፡፡ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ጨምሮ፤ የአህጉሩን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም ቀጣናዊ ውህደትን በተመለከተ ውይይት ይደረጋል፡፡
የአፍሪካ አህጉር የኮሮና ክትባቶችን በፍትሃዊ መንገድ እንዲያገኝ የሚለው ጉዳይ በመሪዎቹ ውይይት እንደሚደረግበት ይጠበቃ፡፡ በአፍሪካ ያላባሩት ግጭቶች ፣ ጽንፈኝነት እና ሽብርተኝነትም በጉባዔው ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል፡፡ ሕብረቱ ቀደም ብሎ እንደገለጸው ወደ ሥራ የገባው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትም በአሁኑ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ሌላ አጀንዳ ነው፡፡
ምንም እንኳን እንደከዚህ ቀደሙ የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት መሪዎች በአዲስ አበባ ባይገኙም አጀንዳዎቹ በቀጥታ በበይነ መረብ ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡ ተሰናባቹ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ያለፈው አንድ ዓመት የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የነበሩ ሲሆን ኃላፊነቱን ዛሬ ለዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አቻቸው አስረክበዋል፡፡ ለሚቀጥሉት 12 ወራት ሕብረቱን የሚመሩት የዲ.አር. ኮንጎ ፕሬዝደንት ፌሊክስ ቺሲኬዲ ኃላፊነቱን ለመረከብ ትናንት ምሽት ነው አዲስ አበባ የገቡት፡፡
የሕዳሴ ግድቡን ድርድርም በቀጣይነት በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር ፕሬዝደንት ፌሊክስ ቺሲኬዲ የሚመሩ ይሆናል፡፡
ተሰናባቹ የሕብረቱ ሊቀመንበር ሲሪል ራማፎዛ 34ኛውን የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ካሉበት ፕሪቶሪያ ሆነው በቀጥታ ከፍተዋል፡፡