45 በመቶ ያህሉ የ6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በደቡብ አፍሪካ ነው የሚታተሙት ተባለ
የህትመት ሂደቱን በተመለከተ ፓርቲዎች እንዲጎበኙ ማድረጉንም ነው ቦርዱ የገለጸው
ቀሪው 55% በዩኤኢ እየታተመ እንደሚገኝ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድምፅ መስጫ ወረቀት የኅትመት ሂደትንና የደኅንነት አጠባበቅ ሥርዓቱን ለፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ማስጎብኘቱን አስታወቀ፡፡
ቦርዱ ከፓለቲካ ፓርቲዎች እና ሚዲያዎች የተወጣጣ የልኡካን ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ በመላክ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመትን እንዲጎበኙ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
በጉብኝቱ ለልዑካኑ የኅትመት ሂደቱን፣ የቴክኒክና የደኅንነት አጠባበቅ ሥርዓቱን በዝርዝር ማሳየት ስለመቻሉ ነው የገለጸው።
በድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ የሚኖረውን የዕጩዎች አደራደር ቅደም ተከተል ቦርዱ የፍትሐዊ አሠራሩ አንዱ ማሳያ አድርጎ እንደሚወስድ ይገልጻል፡፡
ይህንኑ ታሳቢ በማድረግም የቅደም ተከተሉን መወሠኛ ሎተሪ ባሳለፍነው መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ አስጀምሯል፡፡ ከዚያም ወዲህ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ኅትመት ተጀምሯል፡፡
ህትመቱ በሁለት የደቡብ አፍሪካ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) የህትመት ማህበራት የሚከናወን ነው፡፡
በደቡብ አፍሪካ ሬን-ፎርም ኅትመት ማኅበር የሚካሄደው ኅትመት ከአጠቃላይ የምርጫው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች 45% ያህሉን የሚሸፍን ነው፡፡
ህትመቱ የደ/ብ/ብ ፣ የአማራ፣ የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ሕዝበ ውሣኔን ያካትታል።
ቀሪው የህትመቱ 55% ዱባይ በሚገኘው አል-ጉህራር ማኅበር እየተከናወነ ይገኛል እንደ ቦርዱ ገለጻ።
ልዑካኑ የጎበኙትም በደቡብ አፍሪካ በሬን-ፎርም ኅትመት ማኅበር በመካሄድ ላይ ያለውን የህትመት ሂደት ነው፡፡
ጉብኝቱ ለ4 ቀናት የዘለቀ ሲሆን የኅትመት ሂደቱንና የደኅንነት አጠባበቁን በተመለከተ በአታሚው የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ ተሰጥቷቸዋል።
የብልጽግና፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የህብር ኢትዮጵያ ተወካይ (ህብር)፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ እና የሚዲያ አካላት በጉብኝቱ መሳተፋቸውን ቦርዱ አስታውቋል።
የተራዘመውና በመላ አገሪቱ በ11 ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች ሲካሄድ የቆየውየመራጮች ምዝገባ ዛሬ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡
መራጮች ይህን አውቀው ካርድ እንዲወስዱም ቦርዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጭምር ጥሪ አቅርበዋል።
ቦርዱ 31 ነጥብ 7 መራጮች ተመዝግበዋል ሲል ከሳምንት በፊት ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡