“በአዲሱ ዓመት ያልተገቡ ድርጊቶች ተወግደው በመልካም ተግባራትና በአብሮነት መኖር ይገባል”- ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ
አዲሱ ዓመት ሁሉም ተቀራርቦ የሚሰራበት እንዲሁም መመካከርና መተሳሰብ የነገሰበት እንዲሆንም ምኞታቸውን ገልፀዋል
በተጠናቀቀው ዓመት የተስተዋሉ “የማይገቡ” ተግባራትንም ኮንነዋል
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም ዓመቱ ያለፈው ዓመት በኢትዮጵያ የተከሰቱ መልካም ነገሮችን በዘንድሮው ዓመት የምናስቀጥልበት፤ ለሀገራችን ስላም ከመቼውም ጊዜ በላይ የምንሰራበት እና ከመጥፎ ድርጊት የምንቆጠብበት እንዲሆን ሁላችንም የበኩላችንን እንወጣ ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ጥሩ ልማድ የነበራቸውን ሕዝቦች መሆናቸውን አስታውሰው፤ በተጠናቀቀው ዓመት የተስተዋሉ የማይገቡ ተግባራትንም ኮንነዋል።
በአዲሱ የ2014 ዓ.ም ያልተገቡ ድርጊቶች ተወግደው በመልካም ተግባራት፣ በመተዛዘንና በአብሮነት መኖር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በጳጉሜን አምስት ቀናት በከፍተኛ አመራሮች የተተገበሩ መልካም ስራዎች ሁልጊዜም መቀጠል አለባቸውም ብለዋል።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የዛሬ እውቀት መስመሩን እየሳተ ሕዝብን ከመጥቀም ይልቅ ለጉዳት እየዳረገ ነው። እውቀት አለን የሚሉ ሁሉ ለህዝብና ሀገር እድገት ካልሆነ ከማይሃምነት የማይሻል ነው።
በመሆኑም መሪዎች፣ ምሁራኖች ወጣቶችን ሁሉም ለሀገሩ ህዝብ እድገት በጋራ መስራት ይገባዋል ሲሉ መልዕክት አስተላፈዋል።
አዲሱ ዓመት የልማት፣ የሰላም፣ ወደ አንድነት የምንመጣበት፣ ሁሉም ተቀራርቦ የሚሰራበት እንዲሁም መመካከርና መተሳሰብ የነገሰበት እንዲሆንም በመልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል::