አዲሱ ዓመት “ለ30 ዓመታት ኢትዮጵያን የተጣባትን ፈተና” ተገላግለን “አዲስ መንግሥት የምንመሠርትበት እንደሚሆን እምነቴ ነው”- ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲሱን ዓመት በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትን አስተላልፈዋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ወደ አዲሱ ዘመን የምናደርገው ሽግግር የሚጎዱንን አሮጌ ማንነቶች በመጣልና በአዲስ ጠቃሚ ማንነቶች በመተካት መሆን አለበት” ብለዋል
“አዲሱ ዓመት ለ30 ዓመታት ኢትዮጵያን የተጣባትን ፈተና” ተገላግለን “አዲስ መንግሥት የምንመሠርትበት እንደሚሆን እምነቴ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ አዲሱን ዓመት በማስመልከት ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አዲሱ ዓመት በወሳኝ ሀገራዊ ፈተናና ተስፋ መካከል ሆኖ የሚከበር መሆኑን ገልጸዋል ይህ ሲሆን የመጀመሪያም የመጨረሻም እንዳይደለ በመጠቆም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች እንደየ አመጣጣቸው “አሸንፋ” ሺ ዘመናትን በነጻነት መኖሯንም አስታውሰዋል።
“ታሪካችንን ሳያውቁ የሚገጥሙንን ታሪካችንን ዐውቀን እንጠብቃቸዋለን። ለወዳጃችን ወተት፣ ለጠላታችን ዕሬት መስጠት እንችልበታለን። ከቶም ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከማሸነፍ እንጂ ከመሸነፍ ጋራ ተጠርቶ አያውቅም። ከነጻነት እንጂ ከባርነት ጋራ ዝምድና የለውም። ኢትዮጵያ ተፈትና ታውቃለች። ተሸንፋ ግን አታውቅም። ቀጥና ታውቃለች፤ ተበጥሳ ግን አታውቅም። የዘመመች መስላ ታውቃለች፤ ወድቃ ግን አታውቅም” ሲሉም አስቀምጠዋል።
“ይህ አዲሱ ዓመት ለ30 ዓመታት ኢትዮጵያን የተጣባትን ፈተና የምንገላገልበት፣ አዲስ መንግሥት የምንመሠርትበት፣ ከደረሰብን ፈተና የምናገግምበትና ፊታችንን ወደ ኢትዮጵያ ብልጽግና የምናዞርበት እንደሚሆን እምነቴ ነው” ያሉም ሲሆን “አዲሱ ዓመት ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የሚጸናበት፣ ዴሞክራሲያዊ ዕሴቶቻችን የሚጎለብቱበት፣ የጀመርነው ሪፎርም መልክ የሚይዝበት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
በማንነቱ የሚኮራ እና የሚሰራ አዲስ ትውልድ እየተፈጠረ ነው ባሉበት መልዕክታቸው በሀገር ጉዳይ ጣት ከመጠቆም ይልቅ “ከእኔስ ምን ይጠበቃል?” ማለት መጀመር እንዳለበትም ነው የገለጹት፡፡
ወደ አዲሱ ዘመን የሚደረገው ሽግግር “እንደ ሀገር የሚጎዱንን አሮጌ ማንነቶች በመጣልና በአዲስ ጠቃሚ ማንነቶች በመተካት መሆን” አለበትም ብለዋል ጠ/ሚ ዐቢይ።
“ዕንቅፋቶቻችን እየተወገዱ ነው፤ ወደረኞቻችን ሁሉ ድል እየሆኑ ነው። ዘመኑ የኢትዮጵያ ነው። አዲሱ ዓመት የአዲሲቱ ኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያ በአዲሱ የዘመን መጽሐፍ ላይ አዲሱን የብልጽግና ጉዞዋን ትጽፍበታለች። ድሏንና አሸናፊነቷን ትጽፍበታለች። ክብሯንና ታላቅነቷን ትጽፍበታለ ” ሲሉም ነው ያስቀመጡት።
ኢትዮጵያውያን ተደጋግፈው በጋራ ለማደግ እንዲነሱና እርስ በእርስ እንዲተሳሰቡም ጠይቀዋል፡፡
ጠ/ሚ ዐቢይ ዛሬ "ስለ ኢትዮጵያ" እና "Biyya koo" የተሰኙ ሁለት አልበሞችን ሠርተው ያቀረቡ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችን ማመስገናቸው የሚታወስ ነው፡፡