የአለም የካርቦን ልቀት በመጨመር ላይ መሆኑን ተመራማሪዎች ገለጹ
በአለማችን የድንጋይ ከሰል አገልግሎት እየቀነሰ ቢመጣም፣ የካርቦን ዳይኦክሳይድ (CO2) ልቀት ግን በመጨመር ላይ ነው የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደሚሉት፡፡
ቢቢሲ የአለም ካርቦን ፕሮጄክት አመታዊ ትንተናን ጠቅሶ እንደዘገበው በአውሮፓውያኑ 2019 ካርቦን ዳይኦክሳይድ በ 0.6% ጭማሪ ያሳያል፡፡ ጭማሪው በከፍተኛ መጠን እያደገ ከሚገኘው የነዳጅ ፍጆታ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል፡፡ በአለም የመኪና ተሸከርካሪዎች ፍላጎት መጨመር እና ከዚህ ጋር ተያይዞ የዘርፉ ገበያ መድራቱ ደግሞ ለዚህ ከዋና ምክኒያቶች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
በካርቦን ልቀት ቅነሳ ዙሪያ በአውሮፓውያኑ 2015 ከተደረሰው የፓሪስ ስምምነት በኋላ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት በ 4% ጨምሯል፡፡
የድንጋይ ከሰልን መጠቀምም በ 2019 ሊጨምር ይችላል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ነገር ግን ከሌሎች የኃይል አማራጮች ተፈላጊነት ከፍ ማለት ጋር ተያይዞ፣ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በ ዩ.ኤስ. አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት የድንጋይ ከሰልን መጠቀም 10% መቀነሱን ከተመራማሪዎች አንዱ የሆኑት ሮቢ አንድሪው ተናግረዋል፡፡
ይህ መረጃ ይፋ የሆነው 25ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኡ በ ስፔን ማድሪድ እየተካሄደ በሚገኝበት ወቅት ነው፡፡
ከህዳር 22 እስከ ታህሳስ 3/2012 ዓ.ም. የሚካሄደው 25ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ዋነኛ ትኩረት፣ የፓሪሱ ስምምነት በሙላት የሚተገበርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ አሜሪካ ራሷን ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ውጭ ማድረጓ ይታወቃል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ