ሕንድ በዓለም የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር 2ኛ ደረጃን ያዘች
1.3 ቢሊዮን ህዝብ ብዛት ያላት ሕንድ በኮሮና ቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁ የዓለማችን አገራት መካከል 2ኛ ሆናለች
በሕንድ ከቫይረሱ ተጠቂዎች ውስጥ 65 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ45 ዓመት በታች ናቸው ተብሏል
ሕንድ በከፍተኛ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተጠቁ የዓለማችን ሃገራት መካከል 2ኛ ደረጃን ያዘች፡፡
ህንድ ከአሜሪካ ቀጥሎ በከፍተኛ የቫይረሱ ተጠቂነት የተጠቀሰችው ከብራዚል የበለጠ የተጠቂዎች ቁጥር በመያዝ ነው፡፡
በህንድ በዛሬው ዕለት ብቻ 168 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ነው የሃገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ያስታወቀው።
በአጠቃላይ በሕንድ 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች በቫይረሱ ሲጠቁ በብራዚል ደግሞ 13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች በዚሁ ቫይረስ መጠቃታቸው ተገልጿል።
ሕንድ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ከአሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛዋ በኮቪድ የተጠቃች ሃገር ስትሆን ብራዚል በሶስተኛነት ትጠቀሳለች፡፡
በቫይረሱ ከተጠቁ አጠቃላይ ሕንዳዊያን ውስጥ 65 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ45 ዓመት በታች ናቸው።
የሐይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች መስፋፋት እና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መብዛት ቫይረሱ በስፋት እንዲሰራጭ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ባለፉት ሰባት ቀናት ውስጥ ብቻ 873 ሺህ ሕንዳዊያን በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሲሆን በብራዚል ደግሞ 497 ሺህ ዜጎች በዚህ ጊዜ ውስጥ በዚህ ገዳይ ቫይረስ መያዛቸው ተገልጿል።
አሜሪካ ከዓለማችን አገራት በኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ቀዳሚዋ አገር ስትሆን 31 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ሲጠቁ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሆኑ ሰዎች ደግሞ በዚህ ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።
በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን 116 ሺህ ሰዎች ደግሞ ሀይወታቸውን አጥተዋል።
ደቡበ አፍሪካ ሞሮኮ ቱኒዝያ እና ኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ብዛት ቀዳሚዎቹ አገራት ናቸው።
በደቡብ አፍሪካ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሞሮኮ 502 ሺህ ቱኒዝያ 271 ሺህ አንዲሁም ኢትዮጵያ 229 ሺህ ዜጎች በዚህ ቫይረስ መጠቃታቸውን የአፍሪካ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል አስታውቋል።