ልዩልዩ
የብራዚል ፕሬዝዳንት ወረርሽኙን በያዙበት ሁኔታ ላይ በህግ ሊጠየቁ ነው
ትናንት ብቻ 4,200 የቫይረሱ ተጠቂዎች በሞቱባት ብራዚል እስካሁን የ345,000 ሰዎች ህይወት አልፏል
በቦልሶናሮ የወረርሽኝ አያያዝ ላይ ምርመራ እንዲደረግ የሃገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አዟል
በብራዚል ፕሬዝዳንት ጃኤር ቦልሶናሮ እና በመንግስታቸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አያያዝ ላይ ምርመራ እንዲደረግ የሃገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አዘዘ፡፡
የሃገሪቱ ምክር ቤት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ መንግስት እንዲመረመር ጠይቋል፡፡
ብራዚል በከፍተኛ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ቀዳሚወን ስፍራ ትይዛለች፡፡
በርካቶች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን እያጡ ይገኛሉም፡፡
ይህን ተከትሎ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲኖሩ በማሰብ በባለሙያዎች የቀረበውን ምክረ ሃሳብ ፕሬዝዳንቱ ውድቅ አድርገዋል፡፡
ምንም ዓይነት የእንቅስቃሴ ገደቦችን እንደማይጥሉም ነው ቦልሶናሮ ያስታወቁት፡፡
በዚህም ከ81ዱ የሃገሪቱ ምክር ቤት አባላት 32ቱ ፕሬዝዳንቱ እንዲመረመሩ ጠይቀዋል፡፡
የምክር ቤቱን ጥያቄ የተቀበለው የሃገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም መርማሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም ፈቅዷል፡፡
ትናንት ብቻ 4,200 የቫይረሱ ተጠቂዎች በሞቱባት ብራዚል እስካሁን የ345,000 ሰዎች ህይወት በቫይረሱ ምክንያት ማለፉ ተረጋግጧል፡፡
በብራዚል እስካሁን 13.28 ሚሊዬን ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡