የሩሲያ እና ሕንድ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በሞስኮ መወያየታቸው ተገልጿል
ሩሲያ እና ሕንድ የጦር መሳሪያ በጋራ ለማምረት እያሰቡ መሆናቸውን የሩሲያው ላቭሮቭ ገለጹ።
የሩሲያ እና ሕንድ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ባለፉት 10 ወራት ውስጥ ለአምስተኛ ጊዜ በሞስኮ መወያየታቸው ተገልጿል።
ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮቹ ከውይይታቸው በኋላ በሰጡት መግለጫ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ለማምረት ተስማምተዋል ተብሏል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ እና የቴክኒክ ስምምነቶችን በጋራ ለመስራት የተስማሙ ሲሆን ከዚህ ውስጥም ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን በጋራ ማምረትን ያጠቃላል።
እንዲሁም በኑክሌር ሀይል ልማት እና ጠፈር ጉዞ ዙሪያ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውም ተገልጿል።
ሕንድ ከረጅም ዓመት ጊዜ አንስቶ የጦር መሳሪያ ግዢዋን ከምትፈጽምባቸው ሀገራት መካከል ሩሲያ ዋነኛዋ ሀገር ነችም ተብሏል።
ሩሲያም የሕንድ ሰራሽ መድሀኒቶችን ከሚገዙ ቀዳሚ የዓለማችን ሀገራት መካከል አራተኛዋ ሀገር እንደሆነች ተገልጿል።
ሩሲያ ጦሯን ወደ ዩክሬን ከላከችበት ያሳለፍነው የካቲት ወር ጀምሮ ከበርካታ ሀገራት ውግዘት እየደረሰባት ሲሆን ሕንድ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።
የሩሲያን ነዳጅ በገፍ ከሚገዙ ሀገራት መካከልም አንዷ የሆነችው ሕንድ ኬሚካል እና የአፈር ማዳበሪያ ምርቶችንም በስፋት በመግዛት ላይ ትገኛለችም ተብሏል።
ሕንድ ምዕራባዊያን ሀገራት በሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን የተቃወመች ሲሆን ከዩክሬን ጋር ያለውን ጦርነት ለመፍታት መፍትሄው ውይይት እንደሆነም አስታውቃለች።
ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ቢጥሉም ሕንድ ግን የሩሲያ ምርቶችን መግዛቷን እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ሱባራህማንያም ጄይሻንካር ተናግረዋል።