የምርጫው ውጤት ያበሳጫት ቱርካዊ ከባቡር ጋር ተጋጭታ ህይወቷን አጥፍታለች
የ20 አመት ወጣቷ የኤርዶሃን ተፎካካሪ ከማል ክሊችዳሮግሉ ፓርቲ ደጋፊ ነበረች ተብሏል
ከህልፈቷ አስቀድሞ ያስቀመጠችው መልዕክትም በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተዘዋወረ ይገኛል
ቱርክ ከትናንት በስቲያ ያደረገችው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት አሸናፊውን አለየም።
ፕሬዝዳንት ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃንም ሆኑ ዋነኛ ተፎካካሪያቸው ከማል ክሊችዳሮግሉ 50 ከመቶ ድምጽ ማግኘት ባለመቻላቸው ምርጫው በፈረንጆቹ ግንቦት 28 በድጋሚ ይደረጋል።
ይህን ያልሰማችውና ውጤቱ ወደ ኤርዶሃን ማዘንበሉ ያበሳጫት ቱርካዊ በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቷን ማጥፋቷን ተሰምቷል።
ኤርዶሃን ቱርክን መምራት በጀመሩበት አመት መወለዷ የተነገረላት የ20 አመት ወጣት የከማል ክሊችዳሮግሉ ደጋፊ ነበረች።
የምርጫው ውጤት መነገር ሲጀምርና ኤርዶሃን መሪ መሆናቸውን የሚያሳዩ አሃዞች ሲወጡ ስሟ ያልተጠቀሰው ወጣት ህይወቷን የሚያሳጣ ውሳኔ አሳልፋለች፤ ከሚጓዝ ባቡር ጋር ተላትማ መሞት።
ወጣቷ በኢስታንቡል በሚገኘው ያኒካፒ ማርማይ የባቡር ጣቢያ ሃዲድ ውስጥ ዘላ በመግባትና ከሚሄድ ባቡር ጋር በመጋጨት ይህቺን አለም ተሰናብታለች።
ፖሊስ እና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ያደረጉት ርብርብም ሊሳካ አለመቻሉ ነው የተገለጸው።
ቱርካዊቷ ህይወቷን በአሳዛኝ ሁኔታ ከማጥፋቷ በፊት ያስተላለፈችው መልዕክትም በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተዘዋወረ መሆኑን የሊባኖሱ አል አክባር ጋዜጣ አስነብቧል።
“ወጣትነቴን ሁሉንም ነገሬን ቀሙኝ፤ ክሊችዳሮግሉ ይህችን ሀገር ለኑሮ የተመቸች ያደርጋታል ብዬ አስብ ነበር፤ ነገር ግን ከፊቱ መስናክሉን አበዙበት” ይላል የመጨረሻ መልዕክቷ መግቢያ።
“እንደ ሴት ምንም አይነት ነጻነት ተሰምቶኝ አያውቅም፤ ባለፉት ሁለት አመታት ከፍተኛ ድብርት ውስጥ ነበርኩ፤ የስነልቦና አማካሪ ጋርም በተደጋጋሚ እሄዳለሁ፤ በሀገሬ ያለው ፖለቲካ ልጅነቴንም ሆነ ወጣትነቴን ቀምቶኛል” ስትልም ታክላለች።
ትቀጥልናም “እናቴ በየእለቱ እየሰራች ክፍተታችን ለመድፈን ትጥራለች፤ ሁሉም ነገር ግን የሚቻል አይደለም፤ በህይወት ዘመኔ ሁሉ ብቆጥብ ቤት መግዛት አልችልም… እኔ የሙስጠፋ አታቱርክ ልጅ ነኝ፤ ነጻናት መፈክሬ ነው፤ አሁን ሞትን ከመምረጥ ውጭ ነጻነት የለኝም” ትላለች።
ገዥው ፓርቲ “ጀስቲስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት” በሁለት አስርት አመታት ውስጥ ቱርክን ችግር ውስጥ ከመክተት ውጭ የፈየደው ነገር የለም የምትለው ወጣት፥ ቤተሰቦቿን እና ጓደኞቿን ይቅርታ በመጠየቅም ጽሁፏን አጠናቃለች።