ሕንድ የስንዴ ምርት ከሀገሯ ውጪ እንዳይሸጥ እገዳ ጣለች
ሕንድ እገዳውን የጣለችው በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት በሀገሯ የምግብ እጥረት እንዳይከሰት በመስጋት ነው
የአውሮፓ ሀገራት የሕንድን ውሳኔ ዓለም ወደ ከፋ የምግብ ቀውስ እንደሚያመራ ያደርጋል ሲሉ ኮንነዋል
ሕንድ የስንዴ ምርት ከሀገሯ ዉጪ እንዳይሸጥ እገዳ ጣለች።
1 ነጥብ 1 ቢሊየን ህዝብ ብዛት ያላት የሩቅ ምስራቋ ሕንድ በሀገሯ የምግብ እጥረት እንዳይከሰት በሚል የስንዴ ምርት ከሀገር እንዳይወጣ እገዳ ጥላለች።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር (ኔቶ) አቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ከገባች ሶስት ወር ሊሞላት ጥቂት ቀናት ቀርቷታል።
የዓለማችን ቀዳሚ የስንዴ አምራች እና ላኪ የሆኑት ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ጦርነት ማምራታቸው በዓለም የምግብ ዋጋ እንዲንር አድርጓል።
ጦርነቱን ተከትሎም በርካታ የስንዴ አምራች ሀገራት የስንዴ ንግዳቸውን በመከለስ ላይ ሲሆኑ ሕንድም በሀገሯ የሚመረት ስንዴ ወደ ውጭ ሀገራ እንዳይወጣ እገዳ መጣሏን የሀገሪቱ ዜና ወኪል ዘግቧል።
የአውሮፓ ሀገራት በበኩላቸው የሕንድን ውሳኔ የኮነኑ ሲሆን ውሳኔው በዓለም የስንዴ ገበያ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል ሲሉ አክለዋል።
ሕንድ በስንዴ ሽያጭ ላይ እገዳ መጣሏ በተለይም በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የስንዴ አቅርቦት የተቋረጠባቸው የአፍሪካ እና እስያ ሀገራት ሕንድን እንደ አማራጭ ለመጠቀም አስበው ነበር።
የሕንድን ውሳኔ ከተቃወሙ የአውሮፓ ሀገራት መካከል ጀርመን አንዷ ስትሆን ድርጊቱ ዓለም ወደ ከፋ የምግብ ቀውስ እንደሚያመራ በግብርና ሚኒስትሯ በኩል አስታውቃለች።
በመሆኑም ሕንድ እንደ ዓለም ቡድን 20 አባል ሀገር በስንዴ ሽያጭ ላይ የጣለችውን እገዳ በማንሳት ለዓለም ምግብ ዋጋ መረጋጋት የራሷን አስተዋጽኦ እንድታበረክት ጀርመን ጠይቃለች።
ሕንድ በበኩሏ አዲሱ የስንዴ የውጭ ሀገራት እግድ ከዚህ በፊት በሂደት ላይ የነበሩ የስንዴ ግብይቶችን እንደማይመለከት አስታውቃለች።
በሕንድ አንድ ቶን ስንዴ በ25 ሺህ ሩፒ ወይም በ320 ዶላር የሚሸጥ ሲሆን፤ ወደ ውጪ ሀገራት አዲስ የሚደረጉ የስንዴ ግብይቶችን ላልተወሰነ ጊዜ አግዳለች።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በወር 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ዩክሬን ወደ ሌሎች ተለያዩ የዓለማችን ሀገራት ትልክ ነበር።
አብዛኞቹ የዩክሬን ወደቦች በሩሲያ ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ተከትሎ አሁን ላይ 20 ሚሊዮን ቶን ስንዴ በመጋዝኖች ተከዝኖ መቀመጡም ተገልጿል።