በእምባ የታጀበው ስጦታ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስቧል
የህንድ ማድህያ ፕራዴሽ ግዛት ነዋሪው ሩናክ ጉርጃር የሀገሪቱን መገናኛ ብዙሃን ዳግም ተቆጣጥሯል።
ሩናክ እንደቀድሞው በከባድ ወንጀሎች አይደለም የሚዲያዎችን ትኩረት የሳበው፤ ለእናቱ በሰጠው ልዩ ስጦታ እንጂ።
ኡጃይን በተባለችው ከተማ ነዋሪ የሆነው ሩናክ በራሱ ቆዳ የተሰራ ነጠላ ጫማ ነው ለእናቱ በስጦታ መልክ ያበረከተው።
ወንጀል ሰርቶ ለማምለጥ ሲሞክር በፖሊስ እግሩን በጥይት ተመቶ የነበረው ጎልማሳው በማረሚያ ቤት ቆይታው ስለእናቱ አብዝቶ ያስብ እንደነበር ያስታውሳል።
በሂንዱ እምነት ራማ የተሰኘው አማልዕክትን የተመለከቱ ጽሁፎችን ማንበቡም ተጽዕኖ እንዳደረገበት ይናገራል።
“ሎርድ ራማ ለእናቶች ከቆዳችን የሚሰራ ነጠላ ጫማ ብንሰጣቸው ያንስባቸዋል እንጂ አይበዛባቸውም ይል ነበር፤ ይህ ነገር ሁሌም በአዕምሮዬ ሲመላለስ እኔም ለእናቴ ይህን ስጦታ ለመስጠት ወሰንኩ” ሲልም ለኒውስ18 ተናግሯል።
በአደገኛ ወንጀሎች ተሳትፎው የሚታወቀው ሩናክ ጉርጃር ከእስር ሲለቀቅ ለቤተሰቡ ለማንም ሳያሳውቅ ወደ ሆስፒታል ያመራል።
በጭኑ ላይ ያለውን ቆዳ ሀኪሞች በቀዶ ጥገና እንዲያነሱት ካደረገ በኋላም ወደ ጫማ ሰፊ በመውሰድ በቆዳው ነጠላ ጫማ እንዲሰራበት ያደርጋል።
ከሰሞኑ በእናቱ ቤት በመገኘትም ይህን ልዩ ስጦታ አበርክቷል። ሩናክ ለእናቱ ስጦታውን ሲያበረክት እምባውን መቆጣጠር አልቻለም።
ልጃቸው ለሰውነቱ ሳይሰስት ፍቅሩን የገለጸላቸው እናትም ስሜታቸውን መቆጣጠር ሲያቅታቸው ታይቷል።
“ሩናክን የመሰለ ልጅ ስላለኝ እጅግ በጣም እድለኛ ነኝ፤ ልጄን ፈጣሪ ከክፉ ሁሉ ይጠብቅልኝ፤ ህይወቱ ሁሉ ከችግር የራቀና በደስታ የተሞላ እንዲሆንም እመኝለታለው” ሲሉም ተናግረዋል።
ቤተሰቦቻችን ወደ ገነት መውጫ መሰላሎች ናቸው የሚለው ሩናክ ድርጊቱ የሚናገረው ብዙ ቢሆንም በአጭር አገላለጽ መልዕክቱን አስተላልፏል።
“ወላጆቻችን ወደ ገነት መግቢያዎቻችን ናቸው፤ አባት መሰላል ሲሆን እናት ደግሞ መሰላሉን የምንወጣባትና ገነት የምታደርሰን ናት” ብሏል።
የህንዳዊው ጎልማሳ ድርጊት ልጆቻቸውን ብዙ ዋጋ ከፍለው ላሳደጉ እናቶች ምንም መሰሰት እንደማይገባ አሳይቷል በሚል በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች እያጋሩት ነው።