የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ሞስኮ ገቡ
ጠቅላይ ሚንስትሩ በሞስኮ በሚኖራቸው ቆይታ ከቭላድሚር ፑቲን ቀጠናዊ እና ስትራቴጃዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሏል
ህንድ 60 በመቶ የጦር መሳርያ አቅርቦቷን የምትገዛው ከሩስያ ነው
የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ሞስኮ ገብተዋል።
የህንድ ጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ሞስኮ ገብተዋል፡፡
በቅርቡ በህንድ በተደረገ አጠቃላይ ምርጫ ለ3ኛ ግዜ የስልጣን ዘመን ያሸነፉት የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ሞዲ በአዲሱ የስልጣን ዘመናቸው በሚያደርጉት የውጭ ሀገራት የመጀመሪያ ጉብኝት በጦርነት እና በአለምአቀፋዊ ተጽእኖ ውስጥ የምትገኝውን ሩሲያን መርጠዋል፡፡
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ሞስኮ የሚያቀኑት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር በሚኖራቸው ውይይት በቀጠናዊ እና ሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙርያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከቀዝቃው የአለም ጦርነት መጠናቀቅ ማግስት ጠንካራ ወዳጅነት የመሰረቱት ሞስኮ እና ደልሂ በዩክሬን ጦርነት ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው የንግድ ግንኙነታቸው የጠንካራ አጋርነታቸውን መገለጫ ሆኗል፡፡
ከምዕራቡ አለም ጋር ያላት የንግድ እና የፋይናንስ ግንኙነት የተቋረጠባት ሞስኮ ህንድ እና ቻይናን የመሳሰሉ ሀገራት የክፉ ቀን መሻገሪያዎቿ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
አለም በዩክሬን ጦርነት ሩሲያን ሲያወግዝ ተመሳሳዩን እንዲያደርጉ የተጠየቁት ቤጂንግ እና ደልሂ ገለልተኛ አቋም በመያዝ ለሰላማዊ አማራጮች ቅድሚያ እንደሚሰጡ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል፡፡
ሞስኮ ዩክሬንን ከመውረሯ በፊት ቀዳሚዋ የህንድ የጦር መሳርያ አቅራቢ ነበረች። ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም የህንድ 60 በመቶ የጦር መሳርያ ግዢ የሚፈጸመው ከሩሲያ ጋር ነው፡፡
40 በመቶ የነዳጅ ፍጆታዋን ከሩሲያ የምታስገባው ደልሂ በተጨማሪም ከፈተኛ መጠን ያለው የድንጋይ ከሰል ታስገባለች፡፡
ሁለቱ ሀገራት በድንጋይ ከሰል እና በነዳጅ ምርቶች እና በጦር መሳሪያ ላይ ያላቸው ግብይት መጨመሩ ሲገለጽ የምዕራባዊያንን ማእቀብ ተከትሎ ሀገራቱ በየራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት የደረሱት ውሳኔም ወሳኝ እንደሆነም ይጠቀሳል፡፡
በ2023/24 በጀት አመት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት 65 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ነው፤ የንግድ ልውውጡ 50 ቢሊዮን ዶላርን ሲሻገርም ይህ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡
በዚሁ አመት ህንድ ከሞስኮ የምታስገባቸው ምርቶች መጠን በ 1.8 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ደልሂ ወደ ሩሲያ የምትልካቸው ምርቶች ደግሞ በ1.4 በመቶ ከፍ ብሏል። ይህም ሩሲያን የህንድ 4ተኛ ግዙፍ የንግድ አጋር እንድትሆን ያስቻላት መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በነዳጅ እና በተለያዩ ምርቶቿ ላይ እንዲሁም በአጠቃላይ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎቿ ላይ ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ ከፍተኛ ጫና የተጣለባት ሞስኮ ከህንድ እና ከቻይና ጋር የምታደርገው ግብይት ለኢኮኖሚዋ ሳይዳከም መቀጠል ወሳኝ ነው፡፡
በተጨማሪም በአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ የወጣባቸው የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወዳጅ ሀገራት በሞስኮ የሚያደርጉት ጉብኝት በዲፕሎማሲው አለም የሚኖረው ተጽእኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡