የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሀሰን ሸክ መሀሙድ ከወደብ ስምምነቱ ወዲህ ለ2ኛ ጊዜ አስመራ ገቡ
ፕሬዝደንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በዛሬው እለት አስመራ መግባታቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል አስታውቀዋል
ሁለቱ መሪዎች ዛሬ ምሽቱን በሚያካሄዱት ስብሰባቸው የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ጉዳይ ይመክራሉ ብለዋል ሚኒስትሩ
የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሀሰን ሸክ መሀሙድ ከወደብ ስምምነቱ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ አስመራ ገቡ።
ፕሬዝደንት ሀሰን ሸክ መሀሙድ በዛሬው እለት አስመራ መግባታቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል አስታውቀዋል።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው እንደገለጹት ፕሬዝደንት መሀሙድ በአስመራ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተቀብለዋቸዋል።
ሁለቱ መሪዎች ዛሬ ምሽቱን በሚያካሄዱት ስብሰባቸው የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ጉዳይ ይመክራሉ ብለዋል ሚኒስትሩ።
ፕሬዝደንት ሀሰን ሸክ መሀሙድ ወደ ኤርትራ ሲያመሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።
የአሁኑ የፕሬዝዳንት መሀሙድ የኤርትራ ጉብኝት፣ ሶማሊያ የግዛቷ አካል አድርጋ የምታያት ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የወደብ ስምምነት ከፈረመች ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ነው።
ባለፈው የፈረንጆቹ አዲስ አመት እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ የፈረሙት ስምምነት ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቷል።
ከዚያ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የቀይ ባህር ወደብ የመጠቀም ጉዳይ የህልውና ጉዳይ መሆኑን እና ኢትዮጵያ ወደብ ለማግኘት ከቀይ ባህር ተጋሪ ሀገራት ጋር መደራደር እንደምትፈልግ ከገለጹ በኋላ ኤርትራም ብትሆን ቀጥተኛ መልስ ባትሰጥም ከባህር በር እና ወደብ ጋር በያያዙ ጉዳዮች መወያየት እንደማትፈልግ ገልጻ ነበር።
ስምምነቱ አለምአቀፍ ህግን እና የሶማሊያን ሉአላዊነት እንደሚጥስ የገለጸችው ሶማሊያ፣ የኢትዮጵያን አምባሳደር በማባረር ዲፕሎማሲያው ግንኙነት እንዲበላሽ ማድረጓም ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንት ቱርክ፣ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቱን በንግግር በሚፈቱበት ሁኔታ ኢትዮጵያን እና የሶማሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሮች ማናገሯ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባለፈው ሀሙስ በተወካዮች ምክር ቤት በቀረቡበት ወቅት ሶማሊያ መሪዎች ኢትዮጵያን ለመክስስ ወደ ሌላ ሀገር ከሚሄዱ ይልቅ ወደ አዲስ አበባ ቢመጡ የተሻለ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ይህን ተከትሎም ሀሰን ሸክ መሀሙድ ኢትዮጵያ ችግሩን በውይይት ለመፍታት ፍላጎት የላትም ሲሉ መናገራቸው ተሰምቷል።