የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር በቤጂንግ ተገኝተው ቻይና ባቀረበችው የዩክሬን የሰላም እቅድ ዙሪያ ከተወያዩ በኋላ ወደ ዋሸንግተን እንደሚያቀኑ ገልጸዋል
ከፑቲን ጋር የመከሩት የሀንጋሪ መሪ ወደ ዋሸንግተን እንደሚያቀኑ ገለጹ።
የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክተር ኦርባን በቤጂንግ ተገኝተው ቻይና ባቀረበችው የዩክሬን የሰላም እቅድ ዙሪያ ከተወያዩ በኋላ ወደ ዋሸንግተን እንደሚያቀኑ ገልጸዋል።
ሀንጋሪ "አውሮፓን ወደ ገናናነቷ እመልሳለሁ" የሚለውን የአውሮፓ ተች እና የኦርባን አጋር የሆኑትን የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን መፈክር በማስተጋባት የአውሮፓ ህብረት ፕሬዝደንትነቷን ጀምራለች። ከእዚያ ጊዜ ጀምሮ "ለሰላም ተልእኮ" ኪቭን፣ ሞስኮን እና ቤጂንግን ጎብኝተዋል።
ኦርባን ቻይናን የጎበኙት ለዩክሬን ተጨማሪ ወታደራዊ እርዳታ በማድረግ ጉዳይ የሚመክረው የኔቶ ስብሰባ ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ነው። ይህ ጉብኝት የአውሮፓ ህብረት በቻይና የሚመረቱ የኤሌክትሪክ መኪናዎች ወደ ህብረቱ አባል ሀገራት እንዳይገቡ የጣለውን ማዕቀብ ተከትሎ የመጣ ነው።
የትራምፕን ፕሬዝደንት የመሆን እቅድ የሚደግፉት ኦርባን ባለፈው መጋቢት በፍሎሪዳ አግኝተዋቸው ነበር፤ ኦርባን በአሁኑ ጉብኝታቸው በድጋሚ ለመገናኘት እቅድ ስለመያዛቸው የታወቀ ነገር የለም።
የሀንጋሪ መንግስት ኦርባን በማህበራዊ ሚዲያ ስላሳወቁት የአሜሪካ ጉብኝት ተጨማሪ መረጃ ማግኘት አለመቻሉን ሮይተርስ ጠቅሷል።
ኦርባን ሩሲያ በዩክሬን ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተችበት ከፈረንጆቹ የካቲት 2022 ጀምሮ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ለመላክ ፍቃደኛ አልሆነችም። በዚህ ምክንያት ከሩሲያ ጋር የነበራት ቅርብ የኢኮኖሚ ግንኙነት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
ኦርባን በሞስኮ ተገኝተው በፑቲን ጋር የመከሩት ባለፈው አርብ እለት ነበር።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተች በኋላ የአውሮፓ መሪ በሞስኮ ከፑቲን ጋር ሲገናኝ ይህ የመጀመሪያ ነው።
የኦርባን የሞስኮ ጉዞ በሌሎች የአውሮፓ መሪዎች ከፍተኛ ቅሬታ የቀረበበት ሲሆን ዩክሬን ስለጉዞው ቀድማ መረጃ እንዳልደረሳት ገልጻ ነበር።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርዙላ ቮን ደር ለይን በዩክሬን ፍትህ እና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ መንገድ የሚያመቻቸው የ27 የአውሮፓ ሀገራት አንድነት እና ውሳኔ ብቻ ነው ብለዋል።
"መለማመጥ ፑቲንን አያስቆመውም" ሲሉ በትዊተር ገለጻቸው ጽፈዋል።
ኦርባንን በክሬሚሊን የተቀበሉበት ፑቲን ሰላም ጠቃሚ መሆኑን ተናግረው፣ ነገርግን ዩክሬን ሁለት አመት ከግማሽ ያስቅጠረው ጦርነት እንዲያቆም አትፈልግም ብለዋል።
"በተጋጋሚ እንደተናገርኩት ግጭቱን በውይይት ለመፍታት ሁልጊዜም ዝግጁ ነን። ይሁን እንጅ በሌላኛው ወገን (በዩክሬን) በኩል ችግሩን በዚህ ለመፍታት ችላ የማለት ዝንባሌ አለ" ሲሉ ፑቲን የለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ፑቲን ባለፈው ወር ዩክሬን ወደ ኔቶ የመቀላቀል እቅዷን ከተወች እና ሞስኮ የይገባኛል ጥያቄ የምታነሳባቸውን አራት ግዛቶች ሙሉ በሙሉ የምታስረክብ ከሆነ ሞስኮ "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻዋን"እንደምታቆም ተናግረው ነበር። ኪቭ ይህን የፑቲንን ሀሳብ ወዲያውኑ ነበር ውድቅ ያደረገችው።