ወደ ስደተኛ ማቆያነት የተቀየሩት የኒውዮርክ ሆቴሎች በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እያገኙ ነው ተባለ
ከ153 በላይ በኒውዮርክ የሚገኙ ሆቴሎች ሙሉ ለሙሉ ወደ ስደተኞች መጠለያነት መቀየራቸው ተሰምቷል
በቅርቡ በተደረገው የአሜሪካ ምርጫ ክርክር ትራምፕ የባይደን አስተዳደር ስደተኞችን ለማንደላቀቅ የግብር ከፋዮችን ገንዘብ እያባከነ ነው ሲሉ መተቸታቸው ይታወሳል
ወደ ስደተኛ ማቆያነት የተቀየሩት የኒውዮርክ ሆቴሎች በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እያገኙ ነው ተባለ
በኒውዮርክ ከተማ የሚገኙ በርካታ ሆቴሎች ስደተኞችን በማስተናገድ በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ገቢ እያገኙ መሆኑ ተሰምቷል ።
በከተማዋ 193 የሚሆኑ የሰደተኛ ማቆያዎች ሲኖሩ ከዚህ ውስጥ 153 ወይም 80 በመቶዎቹ ሆቴሎች መሆናቸው ታውቋል፤ በእነዚህ ማቆያዎች ውስጥ መነሻቸው ከደቡብ የአሜሪካ ድንበር ያደረጉ ከ65ሺህ በላይ ስደተኞች ይገኛሉ ።
የኒውዮርክ ከተማ አስተዳደር ስደተኞች ለሚያርፉበት እያንዳንዱ ክፍል በአማካይ በቀን 160 ዶላር የሚያወጣ ሲሆን በአንዳንድ ሆቴሎች ከፍያው እስከ 300 ዶላር እንደሚሻገር ነው የተነገረው ።
እስካለፈው ግንቦት ወር ድረስ ለስደተኛ ማቆያዎች ከተማዋ በአጠቃላይ 4.88 ቢሊየን ዶላር ወጭ ስታደርግ 1.98 ቢሊየን ዶላሩ ለሆቴሎች የተከፈለ ነው ተብሏል።
ኒውዮርክ ፖስት እንዳስነበበው ከ16ሺ የሚልቁ የሆቴል ክፍሎች በአሁኑ ወቅት በስደተኞች ተይዘዋል። በኩዊንሰ ፣ ማንሃታን እና ብሩክሊን የሚገኙ ሆቴሎች ከፍተኛ ክፍያ ከተፈጸመላቸው መካከል ይጠቀሳሉ ።
1331 የሆቴል ክፍሎች ላሉት በማንሀታን ለሚገኝው ሮው ኤንዋይሲ ሆቴል እና በአካባቢው ከሚገኙ የጤና ተቋማት ጋር የኒውዮርክ ከተማ አስተዳደር በየወሩ የሚፈጽመው የ5.13 ሚሊየን ክፍያ በመጠኑ ከፍተኛ ነው ተብሏል ።
ሆቴሎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ካፌዎች ፣ የልብስ ሱቆች ፣ ባሮች እና መጠጥ ቤቶች በስራ መቀዛቀዝ ከፍተኛ ቅሬታ እያቀረቡ ነው ።
ለወትሮው በሆቴሎቹ ውስጥ በሚያርፉ እንግዶች ጥሩ ገቢ የሚያገኙት ተጓዳኝ ንግዶች አሁን ላይ ሆቴሎቹ መሉ ለሙሉ ወደ ስደተኛ ማቆያነት በመቀየራቸው ገቢያቸው በመቀዛቀዙ ቅሬታቸውን እየገለፁ ነው።
ከሆቴል ኢንዱስትሪ ጋር የሚያያዙ በርካታ የንግድ እንቅሰቃሴዎች በዚህ ውሳኔ እየተጎዱ ነው ያሉ የከተማዋ ምክርቤት አባላት አስተዳደሩ ስደተኞችን የሚያቆይበት ሌላ አማራጭ እንዲፈልግ በመጠየቅ ላይ ናቸው