የህንድ እና ሩሲያ መሪዎች በኃይል እና በምግብ ገበያ ጉዳይ ተወያዩ
ህንድ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ጦርነት ካላወገዙ ሀገራት መካከል ነች
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ፑቲን የዩክሬንን ቀውስ ለመፍታት ወደ ውይይት እና ዲፕሎማሲ እንዲሄዱ አሳስበዋል
የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አርብ ዕለት በአለም ኢነርጂ እና የምግብ ገበያ ሁኔታ ላይ በስልክ መወያየታቸውን የህንድ ጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ህንድ የሩሲያ ድፍድፍ ዘይት መግዛቷን ቀጥላለች።
"በግብርና ምርቶች፣ ማዳበሪያ እና ፋርማሲ ምርቶች ላይ ያለው የሁለትዮሽ ንግድ እንዴት እንደሚበረታታ ሀሳብ ተለዋውጠዋል" ብሏል መግለጫው። መሪዎቹ የአለም አቀፍ የኢነርጂ እና የምግብ ገበያ ሁኔታን ጨምሮ በአለም አቀፍ ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል።
መግለጫው ሞዲ ፑቲን የዩክሬንን ቀውስ ለመፍታት ወደ ውይይት እና ዲፕሎማሲ እንዲሄዱ አሳስበዋል ብሏል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት የኔቶ ጦር ወደ ቀድሞ የሶቬት ሀገራት እየተስፋፋ ነው፤ይህም ለደህንነቴ ያሰጋኛል በሚል ነበር በዩክሬን ላይ “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” የከፈተችው፡፡ በዘመቻው ዩክሬን ትጥቅ ማስፈታት እና የናዚን አመለካካት ማጥፋት የዘመቻው አላም እንደሆነ ገልጻ ነበር፡፡
አሜሪካን ጨምሮ ምእራባውያን ሀገራት ሩሲያን ያዳክማል ያሉትን ማእቀብ ሁሉ ጥለዋል፤ በመጣልም ላይ ይገኛሉ፡፡ በአንጻሩ ህንድ እና ቻይና ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ጦርነት አላወገዙም፤ በሩሲያ ላይ የተጣለውን ማእቀብ ግን መፍትሄ አይሆንም ሲሉ ተቃውመዋል፡፡