የ82 ዓመቷ አዛውንት በሩጫ አዲስ የዓለም ክብረወሰን አስመዝግበዋል
ባርባራ ሀምበርት የተባሉት አዛውንቷ 125 ኪሎ ሜትርን በ24 ሰዓት ውስጥ ሮጠው ጨርሰዋል
አዘውንቷ የፓሪስና የኒውዮርክ ማራቶንን ጨምሮ በ137 የሩጫ ውድድሮችና በ54 ማራቶኖች ላይ ተሳተፈዋል
የ82 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ የሆኑት ፈረንሳዊቷ ባርባራ ሀምበርት በሩጫ አዲስ የዓለም ክብረወሰን ማስመዝገባቸው ተገለፀ።
ፈረንሳዊቷ አዘውንት ባርባራ ሀምበርት 125 ኪሎ ሜትርን ርቀትን በ24 ሰዓት ውስጥ ሮጠው በመጨረስ አዲስ ክብረወሰን በእጃቸው ማስገባታቸውን ኦዲቲ ሴንተራል ዘግቧል።
ባርባራ ሀምበርት ባሳለፍነው ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ በፈረንሳይ በሪቭ ላ ጋሊርዴ በተካሄደ ሻምፒየንስ ሺፕ ላይ ነው በእድሜያቸው ክልል የተዘጋጀውን ውድድር በ24 ሰዓታት ውስጥ ማጠናቀቅ የቻሉት።
ክብረወሰኑ ከዚህ በፊት በጀርመናዊት አዛውንት ተይዞ የነበረ ሲሆን፤ ጀርመናዊቷ አዛውንት በ24 ሰዓት ውስጥ 105 ኪሎ ሜትሮችን በመሮጥ ነበር ክብረወሰኑን ይዘው የቆዩት።
ፈረንሳዊቷ አዘውንት ባርባራ ሀምበርት በጀርመናዊቷ አዛውንት ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን በ20 ኪሎ ሜትር በማሻሻል ነው በእጃቸው ማስገባት የቻሉት።
ባርባራ ሀምበርት ሩጫ መሮጥ የጀመሩት በ43 ዓመታቸው እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን፤ባለፉት 39 ዓመታት የፓሪስ እና የኒውዮርክ ማራቶንን ጨምሮ በ137 የሩጫ ውድድሮች እና በ54 ማራቶኖች ላይ ተሳተፈዋል።
“በጎዳናዎች ላይ ስሮጥ ነጻነት ይሰማኛል” የሚሉት ፈረንሳዊቷ አዘውንት ባርባራ ሀምበርት፤ “አእምሮዬ ነጻ ይሆናል” ሲሉም ተናግረዋል።
አዘውንቷ ባርባራ ሀምበርት የልጅ ልጅ ልጅ ማየት መቻላቸውን የሚናገሩት አዛውንቷ፤ እስካሁን ታመው መድሃኒት ወስደው እንደማያውቁ እና ጤንነትን ለመጠበቅ ስፖርት መስራት ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ።