በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠው የኢንተርኔት አገልግሎት ተመለሰ
ኢትዮቴሌኮም ዳግም አገልግቱን ለማስጀመር ከፀጥታ አካላት ጋር በመነጋገር ሲሰራ እንደነበረ ይታወሳል
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ኢንተርኔና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ምክንያት ሆኗል
በአማራ ክልል ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተቋረጠው የኢንተርኔት አገልግሎት ዳግም መጀመሩን ነዋሪዎች ተናገሩ።
አል ዐይን አማርኛ ከአማራ ክልል ነዋሪዎች እንዳረጋገጠው የሞባይል ዳታ አገልግሎት መስራት ጀምሯል።
ከሰሞኑ ኢትዮቴሌኮም በአማራ እና በአፋር ክልል ዳግም አገልግሎቱን ለማስጀመር ከጸጥታ አካላት ጋር ንግግር መጀመሩን ለአል ዐይን ገልጾ ነበር።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት ኢንተርኔን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ምክንያት መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ ኢትዮቴሌኮምም ዳግም አገልግሎቱን ለማስጀመር ከሀገሪቱ የጸጥታ ተቋማት ጋር እየተነጋረ እንደሆነ በገለጸ በቀናት ውስጥ አገልግሎቱ ተጀምሯል።
በዚህም መሰረት በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ በደብረታቦር፣ ፣ በወልዲያ፣ በደብረ ማርቆስ፣ በደብረብርሃን፣ በላሊበላ የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩን አል ዐይን አማርኛ ከነዋሪዎች አረጋግጧል።
የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መሳይ ውብሸት ከሰሞኑ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ የተቋረጠውን አገልግሎት ከገና በዓል በፊት ይጀመራል በለው ነበር።
አቶ መሳይ በቅርቡ አገልግሎቱን እንደሚጀመር ቢናገሩም ትክክለኛ ዕለቱን ለመናገር ግን የብዙ ተቋማት ጉዳይ በመሆኑ መናገር እንደማይቻል ተናግረው ነበር።
ከጦርነት ጋር በተያያዘ ከኢንተርኔት በተጨማሪ የባንክ፣ የመብራትና የውሃ አገልግሎቶች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተቋርጠው ቆይተዋል።
ትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር የነበረው ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ባለፈው ጥቅምት 24 አንድ አመት አስቆጥሯል።
የኢትዮጵያ መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የትግራይን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምሮ በርካታ ቦታዎች መቆጣጠር ቢችልም ከ8 ወራት በኋላ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ጦሩን በትግራይ ማስወጣቱ ይታወሳል።
መንግስት ይህን ቢልም፤ ህወሓት የመንግስት ጦር እንዲወጣ ማድረጉን በወቅቱ ገልጾ ነበር። ህወሓት ትግራይን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ አማራና አፋር ክልል በመግባት በርካታ ቦታዎች መቆጣጠርም ችሎ ነበር። ህወሃት በአፋር ክልል አራት፤ በአማራ ክልል ደግሞ በስድስት ዞኖች ወረራ መፈጸሙን ክልሎቹ መግለጻቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሰት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ግንባር ከዘመቱ በኋላ በህወሃት ተይዘው የነበሩ በርካታ የአማራ እና የአፋር ክልል ቦታዎች ነጻ ወጥተዋል።