አይ.ኦ.ኤም በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ 40 ሚሊዮን ዶላር ጠየቀ
ድርጅቱ ለተያዘው ዓመት ስራዎች ከሚያስፈልገው 70 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ያገኘው 28 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው ብሏል
ባለፉት 20 ቀናት ከ41 ሺህ በላይ ሰነድ አልባ ዜጎች ከሳውዲ አረቢያ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል
ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ 40 ሚሊዮን ዶላር ጠየቀ።
አይ.ኦ.ኤም ለአል ዐይን አማርኛ በላከው መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉ የትግራይ እና አማራ ከልሎች በተፈጠረው ጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎችን እየረዳ መሆኑን ገልጿል።
ይሁንና ጦርነቱ አሁንም እየተካሄደ በመሆኑ ከዚህ በፊት ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በድርጅቱ ስር ያሉ እና አሁንም እየተፈናቀሉ ያሉ ተፈናቃዮችን ለመርዳት 40 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ድርጅቱ ገልጿል።
እንደ ድርጅቱ ገለጻ አሁን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ ሲሆን የኮሮና ቫይረስ፤ጦርነት እና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳቶች ተጨማሪ ተፈናቃዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ የድርጅቱ ሃላፊ ማውሪን አቼንግ ተናግረዋል።
ድርጅቱ አሁን ላይ በትግራይ ክልል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች በጦርነቱ ንብረታቸው ለወደመባቸው፣ የደህንነት ችግር ላጋጠማቸው ተፈናቃይ ሴቶች፣ ህጻናት እና ሌሎች ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የአደጋ ተጋላጭ ዜጎች ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
ድርጅቱ ለነዚህ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የምግብ፤መጠለያ፤የንጽህና ቁሳቁስ እና ሌሎች የጤና ድጋፎችን እያደረገ እነደሚገኝም ገልጿል።.
ለተፈናቃዮቹ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ በተያዘው ዓመት 70 ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልገው ቢሆንም ከለጋሽ ተቋማት ያገኘው ገንዘብ 28 ሚሊዮን ዶላር ብቻ በመሆኑ ተጨማሪ 40 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ሲል በመግለጫው አስጠንቅቋል።
በትግራይ ክልል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ መብት እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውም ድርጀቱ አክሏል።
ድርጅቱ ባለፉት አራት አመታት ውስጥ በሳውዲ አረቢያ ህጋዊ የጉዞ ሰነድ እና የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው ቀርቶ ህይወታቸውን በእስር ቤት ይመሩ የነበሩ 400 ሺህ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉንም አስታውቋል።
ከተመላሾቹ ውስጥ 34 ሺህ 511 ያህሉ ወንዶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ወንዶች መሆናቸውን የድርጅቱ ሪፖርት ያስረዳል።
ባለፉት 20 ቀናት ከ41 ሺህ በላይ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ከሳውዲ አረቢያ ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን ትግራይ፤አማራ፣ እና ኦሮሚያ ክልሎች በቅደም ተከተል ብዙ ነዋሪዎቻቸው የተሰደዱባቸው እና አሁን የተመለሱባቸው ክልልች ናቸው።