አይኦኤም “በሰሜን ኢትዮጵያ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች” መፈናቀላቸውን ሪፖርት አደረገ
ከተፈናቃዮቹ “80 በመቶ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው”ብሏል አይኦኤም
በትግራይ በጸጥታ ችግር ምክንያት ተፈናቃዮች ያሉባቸው በርካታ ቦታዎች ለሰብአዊ አጋሮች ተደራሽ አለመሆናቸውን አይኦኤም ሪፖርት አድርጓል
በአሁኑ ሰዓት በትግራይ ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች ከሚገኙ 178 ተደራሽ አካባቢዎች ከ1 ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች መፈናቀላቸውን ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት(አይኦኤም) በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ በትግራይ ግጭት ከተፈጠረ በኋላ በክትትል ማትሪክስ ቴክኒክ መሰረት የዳሰሳ ጥናት ማድረጉን ገልጿል፡፡
እንደ አይኦኤም ጥናት ከሆነ ታድያ ፤እ.ኤ.አ ከመጋቢት 2 እስከ መጋቢት 23/2021 ቀን በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት መሰረት በትግራይ ክልል ወደ 1 ሚሊዮን 592 ፣ በአፋር ክልል ሌላ 45,343 እና በአማራ ክልል 18,781 ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ ተረጋግጧል፡፡
መረጃው እንደሚያመለክተው ተፈናቃዮች ሰብዓዊ እርዳታ ለመፈለግ እና አስፈላጊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ከተሞች እየተሰደዱ ነው፡፡ በአከባቢው በአይኦኤም የተካሄደው እንደዚህ ዓይነት ጥናት ሲካሄድ ለአራተኛ ጊዜ ነው ፡፡
መረጃው ለድርጅቱ ዲጂታል የመሬት አቀማመጥ ሞዴል (ዲቲኤም) ቀያሾች ፤ተደራሽ በሆኑ አካባቢዎች የተፈናቀሉትን ብቻ የሚያመላክት እንደሆነም ነው አይኦኤም በድህረ-ገፁ ላይ ባወጣው ሪፖርት ያስነበበው፡፡
“በትግራይ ክልል በሰሜን ምዕራብ ፣ በማዕከላዊ ፣ በምስራቅ እና በደቡባዊ ዞኖች የሚገኙ በርካታ አካባቢዎች አሁንም ድረስ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ለሰብአዊ አጋሮች ተደራሽ አይደሉም” ብሏል አይኦኤም፡፡
445,309 የሚሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች በሽረ ከተማ እንደሚገኙ፤ እነዚህም በትምህርት ቤቶች፣ በክፍት ቦታዎች፣ በመጠለያዎችና ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንደሚኖሩ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ የምዕራብ እና የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ነዋሪወች መሆናቸውን የገለፀው የድርጅቱ ሪፖርት፤ ሌሎች ከፍተኛ መጠን ያላቸው ተፈናቃዮች በተለያዩ ከተሞች ማለትም በአድዋ 129 ሺህ 524 ፣በመቀሌ 126 ሺህ 267 ፣ በአዲግራት 100 ሲህ 168 እንዲሁም በአክሱም 60 ሺህ 115 ተፈናቃዮች ይገኛሉ ብሏል፡፡
በተደረገው የዳሰሳ ጥናት መሠረት ህይወት አድን የምግብ ድጋፍ ፣ የአስቸኳይ ጊዜ መጠለያ ፣ እንደ አልጋ ልብስ እና የወጥ ቤት እቃዎች ያሉ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች፣ የጤና አገልግሎቶች ፣ የውሃ አቅርቦት ፣ የአካባቢ ጽዳትና ንፅህና ጉዳይ እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ እና ጥበቃ አገልግሎቶች ተፈናቃዮቹ ከሚጠይቅዋቸው በጣም አስቸኳይ ፍላጎቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ 75 ጣቢያዎች የምግብ ስርጭት እንዳላገኙ የሚገልፀው አይኦኤም የዳሰሳ ጥናት ከተደረገባቸው አከባቢዎች 80 በመቶ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ጠቁመዋል፡፡
አይኦኤም ችግሩ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ የሰብአዊ እና የተፈናቃዮችን ሁኔታ በየወሩ በየአከባቢው በተመሰረቱ ምዘናዎች በመከታተል ላይ ሲሆን ፤ በዚህም የተፈናቃዮችን ቁጥር ፣ ቦታዎቻቸውን እና የሚያስፈልገውን የሰብዓዊ ምላሽ ለማሳወቅ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የተፈናቀሉ ሰዎች ፍላጎቶች ተለይተው አስፈላጊውን ምላሽና ሽፋን እስኪያገኙ ድረስ አይኦኤም በሰሜን ኢትዮጵያ የሚያደርገው የክትትል ማትሪክስ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበትም ነው በሪፖርቱ የተገለጸው፡፡
እ.ኤ.አ ከ2018 ጀምሮ ይህ ማትሪክስ በኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ ተፈናቃዮች ቁጥር ይፋዊ ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው፡፡ ዲቲኤም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር እንደሚሰራ ይታወቃል፡፡