በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ ተግባራት እየጨመሩ መምጣታቸውን ተመድ ገለፀ
የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ/OCHA) ትግራይ የተመለከተ ሪፖርት አውጥቷል
እስካሁን ድንበር አቋርጠው ወደ ሱዳን የገቡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር 62,500 መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ/OCHA) ትግራይን የተመለከተ ሪፖርት ዛሬ ሚያዝያ 4 ቀን 2913 ዓ.ም አውጥቷል፡፡
ሪፖርቱ በትግራይ የተፈጠረውን ሁኔታ ተከትሎ በክልሉ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ መከሰቱን አስታውሷል፡፡
ይሁን እንጂ ችግሩን ለማቃለል በኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ በዓለም አቀፍ ተቋማት እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት፣ ለዜጎች የሚደረገው ‘ሰብዓዊ እርዳታ’ እየጨመረ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ባለፈው ሚያዝያ 7 መግለፃቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ እርዳታ ለማዳረስ የሚያስችሉ የተሻሉ ሁኔታዎች መፈጠራቸውንም እንዲሁ፡፡
በሽረ ከተማ ብቻ -350,000 ተፈናቃዮች መኖራቸውን የጠቆሙት ከፍተኛ ኮሚሽነሩ “በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች እና ተጠልለው የነበሩ ስደተኞች ወደ ከተሞች ተፈናቅለዋል፡፡ በመሆኑም ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት በእጅጉ ሊጠናከርና ሊሰፋ ይገባል” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
እንደ ፈረንጆቹ መጋቢት 18/2021 የተ.መ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን /UNHCR/ እና አጋሮቹ ፣ ከህዳር 2020 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሺመልባና ሕፃፅ የስደተኛ መጠለያ ካምፖችን መጎብኘታቸውንም የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ/OCHA/ ባወጣው ሪፖርት ጠቅሷል፡፡ ሁለቱም መጠለያ ካምፖች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውንና ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን እንዳጣሩም እንዲሁ፡፡
እስከ ፈረንጆቹ ሚያዝያ 5/2021 ብቻ 62,500 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ድንበር አቋርጠው ወደ ሱዳን መግባታቸውንም ነው ሪፖርቱ የሚያመለክተው፡፡ ሪፖርቱ አክሎም ከስደተኞቹ 41,000 የሚሆኑት መጀመሪያ ከነበሩበት ወደ ሌላ ቦታ የተዛወሩ ሲሆን ከነዚህም 20,572 የሚሆኑት ወደ ኡም ራኩባ መጠለያ ካምፕ እንዲሁም 20,609 ወደ ቱናዲባ መጠልያ ካምፕ የተዛወሩ መሆናቸውን አትተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን/UNHCR/ እና የዓለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም /WFP/ ለኡም ራኩባ እና ቱናዲባ መጠልያ ካምፖች የሚያገለግሉ የ56 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያለው መንገድ ለመገንባት እንዲሁም የጎርፍ አደጋንን ለመከላከል ከዝናብ ወራት በፊት ሰፊ የፍሳሽ ማስወገጃ ስራዎችን ለማከናወን የጋራ እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም ኦቻ (OCHA) በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡