ኢራን ሚሳይሎችን እና ድሮኖችን ለሩሲያ ለማቅረብ መስማማቷን ገለጸች
መሳሪያዎቹ መሬት በመሬት ተተኩሰው ከ300 እና 700 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ያለን ኢላማ ይመታሉ
ኢራን ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ለማቅረብ መስማማቷ አሜሪካን እና ምእራባውያን ሀገራት ሊያናድድ ይችላል ተብሏል
ኢራን መሬት በመሬት የሚተኮሱ ሚሳይሎችን እና ተጨማሪ ድሮኖችን ለሩሲያ ለመስጠት መስማማቷን ሮይተርስ ሁለት የኢራን ከፍተኛ ባለስልጣናትን እና ሁለት ድፕሎማቶችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ይህ ኢራን እርምጃ አሜሪካን እና ሌሎች ምእራባውያን ሀገራት ሊያናድድ ይችላል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ስምምነቱ የተደረሰው የኢራን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት ሞሀመድ ሞክቤር እና ሁለት ከፍተኛ ባለስልጣናት መሳሪያው በሚቀርብበት ጉዳይ ለመወያየት በሞስኮ ጉብኝት ባደረጉበት በፈረንጆቹ ጥቅምት ስድስት ነው፡፡
ሩሲያ ተጨማሪ ድሮኖችን እና ኢላማቸው የተሻሻለ ባለስቲክ ሚሳይሎችን በተለይም ፋተህ እና ዞልፋገርን መጠየቋን አንድ የኢራን ባልስልጣና መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
ኢራን ከሩሲያ ጋር ከመሬት ወደ አየር የሚተኩስ የአጭር ርቀት ሚሳይሎችን ለመስጠት አንድ ምእራባዊ ባለስልጣን አረጋግጠዋል፡፡ ኢራን ለሩሲያ ልትሰጥ ካሰበቸው ውስጥ ሻሃድ-136 ከአየር ወደ አየር የሚተኩስ ድሮን አንደኛው መሆኑ ተገልጿል፡፡
ፋተህ-110 እና ዞልፋገር ኢራን ሰራሽ የአጭር ርቀት ሚሳይሎች ሲሆኑ መሬት በመሬት ተተኩሰው ከ300 እና 700 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ያለን ኢላማ ይመታሉ፡፡
የኢራኑ ዲፕሎማት ኢራን የጦር መሳሪያ ለሩሲያ ማስተላለፏ በፈረንጆቹ 2015 የተደረሰውን የተመድን የጸጥታው ም/ቤት ውሳኔን ይጥሳል የሚለውን የምእራባውያን አቤቱታ አይቀበሉትም፡፡
የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማእቀብ ሊጥል አንደሚችል ቀደም ሲል አስጠንቅቋል፡፡